Sunday, September 22, 2024
spot_img

የአዲስ አበባ ፖሊስ ለቅቄዋለሁ ያለው የአሐዱ ሬዲዮ ዜና አርታኢ ያለበትን ማወቅ እንዳልቻሉ ቤተሰቦቹ ገለጹ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ታኅሣሥ 5 2014 በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከእስር ተለቋል የተባለው የአሐዱ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ዜና አርታኢ ክብሮም ወርቁን ያለበትን ማወቅ እንዳልቻሉ ቤተሰቦቹ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ድረ ገጽ እንደዘገበው፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ክብሮምን ከእስር መፍታቱን ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢያሳውቅም፣ ቤተሰቦቹ በበኩላቸው ክብሮም ከ26 ቀናት በፊት በፍርድ ቤት ከእስር እንዲለቀቀ ቢወሰንለትም እስካሁንም ያለበትን እንደማያውቁ ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል።

ጋዜጠኛው ከእስር አልተፈታም የሚል እምነት ያላቸው የክብሮም ቤተሰቦች፤ ጉዳዩን ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የወሰዱት ባለፈው ህዳር ወር አጋማሽ መሆኑን ያስታወሰው ዘገባው፣ በጠበቃው አማካኝነት ለፍርድ ቤቱ የቀረበው አቤቱታ፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ‹‹የፍርድ ቤት ውሳኔ ባለማክበር፣ ግለሰቡን በኃይል አስገድዶ በመያዝ ከእስር ቤት እንዳይፈታ ከልክሏል›› የሚል እንደነበርም ተመላክቷል፡፡

ጠበቃው በመጀመሪያ አቤቱታቸውን ያቀረቡበት የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ የፍትሃብሔር ችሎት አቤቱታውን ወድቅ ማድረጉን ተከትሎ፣ የጋዜጠኛው ጠበቃ በዚህ የፍርድ ቤት ውሳኔ ቅር በመሰኘት ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ብለዋል።  

የጋዜጠኛውን ክስ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ኅዳር 28፤ 2014 መመልከት የጀመረው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ‹‹ግለሰቡን ለምን እንዳልፈታው መልስ ይዞ እንዲቀርብ›› ትዕዛዝ በማስተላለፉ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ትላንት ታኅሣሥ 4፤ 2014 ለፍርድ ቤቱ በጽሑፍ ባቀረበው መልስ ክብሮም በኮሚሽኑ በሚገኙ የተጠርጣሪ ማቆያም ሆነ በኮሚሽኑ እውቅና ስር የሌለ መሆኑን ገልጿል። የፖሊስ ኮሚሽኑን ወክለው ፍርድ ቤት የተገኙት ነገር ፈጅም፤ ጋዜጠኛው ኅዳር 9፤ 2014 ከእስር መፈታቱን እና በአዲስ አበባ ፖሊስ ቁጥጥር ስር የሌለ መሆኑን በቃል አስረድተዋል፡፡

የጋዜጠኛው ጠበቃ አቶ ጥጋቡ ደሳለኝ በበኩላቸው ፖሊስ ጋዜጠኛውን ፈትቻለሁ ባለበት ዕለት፤ ደንበኛቸው አለመፈታቱን ለፍርድ ቤት ገልጸዋል። ጋዜጠኛው በቁጥጥር ስር ሲውል ፖሊስ በኤግዚብትነት የያዛቸው የጋዜጠኛው የድምጽ መቅጃ፣ የሞባይል ስልክ፣ የባንክ ደብተር እና ሌሎች ንብረቶች አሁንም በፖሊስ እጅ እንደሚገኙ ከመርማሪ ፖሊስ ማረጋገጣቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።

በችሎቱ ላይ የተገኙት የጋዜጠኛው አባት በፍርድ ቤት የተወሰነውን 15 ሺህ ብር የዋስትና ገንዘብ ከከፈሉ በኋላ ልጃቸው በትዕዛዙ መሰረት አለመፈታቱን ተናግረዋል። ፖሊስ ክብሮምን ፈትቸዋለሁ ባለበት ቀን፤ ከኮሚሽኑ ቅጥር ግቢ በሚኒባስ ተሸከርካሪ ወደ ሌላ ስፍራ ስለመወሰዱ መረጃ እንዳላቸውም አስረድተዋል። አቶ ወርቁ አብርሃ ልጃቸውን ለአንድ ወር ገደማ እንዳላዩት እና የት እንዳለ እንደማያውቁም ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ነግረውኛል ብሏል፡፡

ፍርድ ቤቱ በትላንት ውሎው የይግባኝ ባይ ጠበቃ በፖሊስ መልስ ላይ፤ የመልስ መልስ በሬጂስትራር በኩል እንዲያቀርቡ ለነገ ረቡዕ ታኅሣሥ 6፣ 2014 ትዕዛዝ ሰጥቷል። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን መልስ እና የይግባኝ ባይን የመልስ መልስ ለመርመርም ለታኅሣሥ 12 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። 

ጋዜጠኛ ክብሮም ‹‹ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት›› ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር የዋለው ከ48 ቀናት በፊት ጥቅምት 16፤ 2014 ነበር።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img