Sunday, September 22, 2024
spot_img

የአሜሪካው ልዩ መልዕክተኛ በኢትዮጵያ ጉዳይ ለመምከር ቱርክን ጨምሮ ወደ ሦስት አገራት ጉዞ ሊያደርጉ ነው

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ኅዳር 30፣ 2014 ― የባይደን አስተዳደር የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ልዩ መልእክተኛው አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን በኢትዮጵያ ጉዳይ ለመምከር ወደ ቱርክ፣ የተባበሩት ዐረብ ኤሜሬት እና ግብጽ ጉዞ ሊያደርጉ ነው፡፡

የዋይት ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት በነገው እለት ጉዞ የሚጀምሩት ፌልትማን፣ በአገራቱ ጉዟቸው በኢትዮጵያ ያለው ግጭት በሰላማዊ መንገድ የሚፈታበት መንገድ ላይ ይመክራሉ፡፡

የዋይት ሐውስ ቃል አቀባዩ ኔድ ፕራይስ፣ የአሜሪካ መንግሥት ለዚህ ግጭት ወታደራዊ እርምጃ መፍትሔ አይሆንም ብሎ እንደሚያምን ገልጸው፣ የፌልትማን ተልዕኮም ግጭቱን ለማስቆም ብቸኛው አማራጭ በማድረግ ተፋላሚ ኃይሎች ያለ ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁመው ልዩነቶቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ ለማስቻል ነው።

ለኢትዮጵያ ጉዳይ መፍትሔ ለመሻት ወደ ሦስቱ አገራት ያቀናሉ የተባሉት የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ልዩ መልእክተኛው አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን፣ ከሁለት ሳምንታት በፊት አዲስ አበባ የነበሩ ሲሆን፣ በቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ከሕወሓት መሪዎች ጋር መወያየታቸውን ለመገናኛ ብዙኃን ተናግረው ነበር፡፡  

ፌልትማን በወቅቱ በኢትዮጵያ የነበራቸው ጉብኝት አጠናቀው ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ አላማ የህወሓት ኃይሎችን ከአማራ እና ከአፋር ክልሎች ማስወጣት መሆኑን ገልጸው ነበር፡፡

ይህንኑ ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ግንባር መዝመታቸውን ያስታወቁ ሲሆን፣በሕወሓት ተይዘው የነበሩ በርካታ የአማራ እና አፋር ክልል አካባቢዎችንም የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች መቆጣጠር ችለዋል፡፡ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በአሁኑ ወቅት እስከ ሐይቅ ከተማ ድረስ መድረሳቸው የተነገረ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ወደ ቢሮ መመለሳቸውን አስታውቀዋል፡፡

አሁን ፌልትማን ለመፍትሔ ይጓዙባቸዋል ተባሉት አገራት መካከል ቱርክና የተባበሩት አረብ ኤምሬት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግስት ጋር የቀረበ ግንኙነት እንዳላቸው ይነገራል፡፡

እነዚህ አገራት በትግራይ ጦርነት ለመንግስት ወታደራዊ ቁሳቁስ አቅርበዋል በሚል ከሕወሓት በኩል ስሞታ የሚቀርብባቸው ቢሆንም፣ በአደባባይ አስረጂ አልቀረበም፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img