Saturday, May 18, 2024
spot_img

የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት የማሸማገል እንቅስቃሴ እያደረጉ የሚገኙት ኦባሳንጆ፤ ከሁለቱም አካላት አሉታዊ ምላሽ እንዳላገኙ ተናገሩ

 

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ጥቅምት 30፣ 2014 ― ከአንድ ዓመት በፊት በትግራይ ክልል ተጀምሮ ወደ አጎራባች አፋር እና አማራ ክልሎች የተስፋፋውን የፌዴራል መንግስት እና የሕወሓት ጦርነትን ለማሸማገል እንቅስቃሴ እያደረጉ የሚገኙት የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛው ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ፣ ከሁለቱም አካላት አሉታዊ ምላሽ እንዳላገኙ ተናግረዋል፡፡

የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት እሑድ ጥቅምት 28፣ 2014 ወደ መቐለ ያቀኑ ሲሆን፣ ወደ መቐለ ከመጓዛቸው በፊት ከፕሬዝደንት ሳሕለ ወርቅ ዘውዴ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንዲሁም ከኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት ሺመልስ አብዲሳ ጋር ተገናኝተው መወያየታቸውን ትላንት ምሽት በተካሄደው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ውይይት ላይ አስረድተዋል። 

ኦባሳንጆ በኢትዮጵያ ተፋላሚ አካላት መካከል ለሚያካሄዱት ሽምግልና ተቀባይነት አላገኘም በሚል ጭምጭምታዎች እንደነበሩ ያስታወሰው ቢቢሲ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዐሕመድ በጨዋነት አስተናግደውኛል እንዳሉት ያስነበበ ሲሆን፣ ወደ መቐለ ሲያቀኑ የተቀበሏቸው ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤልም አንድ የአፍሪካ መሪ ሊያስተናግደኝ በሚችለው መንገድ አስተናግደውኛል እንዳሉት ዘግቧል፡፡

በትላንትናው የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባው ላይ በአዲስ አበባ ቆይታቸው ከፌደራል መንግሥት ባለስልጣናት እና ከኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት ጋር ያደረጓቸው ውይይቶች ፍሬያማ እንደነበሩ ያብራሩት ኦባሳንጆ፣ በአዲስ አበባ እና በመቐለ ባደረጓቸው ውይይቶችም ቢሆን ባለስልጣናቱ ‹‹ልዩነቶቻቸው ፖለቲካዊ መሆናቸውን እና ፖለቲካዊ መፍትሔ እንደሚሹ በተናጠል መስማማታቸውን›› ለጸጥታው ምክር ቤት አስረድተዋል።

ኦባሳንጆ አያይዘውም የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ሁለቱም አካላት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ፖለቲካዊ ውይይት እንዲጀምሩ ጠንካራ ግፊት እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል። ወደ ኢትዮጵያ ከገቡበት ባለፈው ሐሙስ ጥቅምት 25፣ 2014 ጀምሮ የፌዴራል መንግስት እና የሕወሓት መሪዎችን ያገኙት ኦባሳንጆ፣ በዛሬው እለት ማክሰኞ ወደ አፋር እና አማራ ክልሎች የማቅናት እቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

ጋብ ብሎ ከቆየበት በጥቅምት የመጀመሪያ ቀን ዳግም ላገረሸው ጦርነት ለማፈላለግ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ በተመሳሳይ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የአሜሪካ መንግስት የምሥራቅ አፍሪካ ልኡኩ ጄፍሪ ፌልትማን፣ በአዲስ አበባ ቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር መነጋገራቸውን የዋይት ሐውስ ቃል አቃባይ ኔድ ፕራይስ ገልጸዋል፡፡ ዐርብ ጥቅምት 26፣ 2014 ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተወያዩት ፌልትማን በማግስቱ ወደ ናይሮቢ አቅንተው ከኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር የተገናኙ ሲሆን፣ ትላንት ሰኞ በድጋሚ ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል። 

አንድ ዓመት በተሻገረው ጦርነት፣ የሕወሓት ኃይሎች የአማራ ክልል ከተሞች የሆኑትን ደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞችን አልፈናል ማለታቸውን ተከትሎ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ከሚለው ታጣቂ ቡድን ጋር ወደ አዲስ አበባ የማቅናት እቅድ እንዳላቸው ሲናገሩ የቆዩ ቢሆንም፣ በትላናትናው እለት ከዶይቸ ቬለ ጋር ቆይታ ያደረጉት ቃል አቀባዩ ጌታቸው ረዳ ‹‹በትግራይ ክልል ላይ የተጣሉ ዕቀባዎች ከተነሱ እና  የተቋረጡ አገልግሎቶች ከተመለሱ›› ሕወሓት የተኩስ አቁም ለማድረግ እና ከፌዴራል መንግስት ጋር ለመደራደር ፍቃደኛ መሆኑን ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡

በመንግሥት በኩል ለአቶ ጌታቸው ንግግር ምላሽ ባይሰጥም፣ ባለፈው ሐሙስ ጥቅምት 25፣ 2014 ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ ማብራሪያ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ የአፍሪካ ቀንድ ተወካዩ ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ ምን ዓይነት መፍትሔ ይዘው እንደሚመጡ መንግሥት እየጠበቀ ነው ብለው ነበር፡፡

በፌዴራል መንግስት እና በሕወሓት መካከል እየተካሄደ የሚገኘው ጦርነት የበርካቶችን ሕይወት ሲቀጥፍ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሏል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img