አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ኅዳር 29፣ 2014 ― የአፍሪካ ኅብረት የምሥራቅ አፍሪካ ልዩ መልዕክተኛ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ወደ ናይሮቢ በማቅናት ከኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር መክረዋል።
ኦባሳንጆ እና ኡሁሩ በቆይታቸው ቀጣናዊ እንዲሁም አህጉራዊ ጉዳዮችን ማንሳታቸውን የኬንያ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት በትዊተር ገጹ አስታውቋል።
የፕሬዝዳንቱ ጽሕፈት ቤት በቆይታቸው የኢትዮጵያን ጉዳይ ማንሳታቸውን ባይጠቅስም፣ የአፍሪካ ቀንድ ልኡኩ ኦባሳንጆ እና የኬንያ ፕሬዝዳንት በቅርብ ጊዜያት በኢትዮጵያ ላለው ግጭት ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ ለመፈለግ እንቅስቃሴ እያደረጉ ስለመሆናቸው መነገሩ አይዘነጋም።
ከሁለቱ ባለሥልጣናት መካከል ኦባሳንጆ በተለያየ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ በማቅናት የፌዴራል መንግስት እና የሕወሓት መሪዎችን ሲያገኙ፣ ኡሁሩ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከፕሬዝዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ ጋር ተነጋግረዋል።