አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ኅዳር 28፣ 2014 ― በአሜሪካና ዩናይትድ ኪንግደም የሚገኙ በደርዘን የሚቆጠሩ የሮሂንጃ ስደተኞች በማኅበረሰባቸው ላይ የጥላቻ ንግግር እንዲሠራጭ ፈቅዷል በማለት ግዙፉን የማህበራዊ መድረክ ፌስቡክን ከሰዋል።
ስደተኞች በክሳቸው የፌስቡክ መድረኮች በሮሂንጃ ማህበረሰብ ላይ ጥቃት አበረታተዋል በማለት የጠየቁት የ150 ቢሊዮን ፓውንድ ካሳ ነው፡፡
አብዛኛው ሕዝቧ የሂንዱ እምነት ተከታይ በሆነው በቀድሞዋ በርማ ወይም የምይናማር በአውሮፓውያኑ 2017 በተደረገ ወታደራዊ ዘመቻ ከ10 ሺህ የሚልቁ የሮሂንጃ ሙስሊሞች ተገድለዋል።
በእንግሊዝ አንዳንድ የሮሂንጃ ስደተኞችን ወክሎ እየተከራከረ ያለው የብሪታኒያ የህግ ተቋም ለፌስቡክ የፃፈውን ደብዳቤ ተመልክቻለሁ ያለው ቢቢሲ፣ ኩባንያው ‹‹በደቡብ ምሥራቅ እስያ በምትገኝ ትንሽ ሀገር ውስጥ ለተሻለ የገበያ ትስስር በሮሂንጃ ሕዝብ ሕይወት ለመገበያየት ፈቃደኛ ነው›› ማለቱን መግለጻቸውን አስነብቧል፡፡
በተጨማሪም በአውሮፓውያኑ 2013 ‹‹ሂትለር አይሁዶች ላይ ባደረገው መንገድ እነሱን ልንዋጋቸው ይገባል›› በማለት በሬውተርስ የዜና ወኪል ባደረገው ምርመራ ላይ የወጣውን ይህን ጽሑፍ ጨምሮ ሌሎች የፌስቡክ ፅሁፎችን ዋቢ ማድረጋቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
በፌስቡክ ከተሠራጩ ጽሑፎች መካከል ‹‹ነዳጅ አፍስሱና እሳት ለኩሱባቸው አላህን በፍጥነት ይገናኛሉ›› የሚል እንደሚገኝበትም ተገልጧል፡፡
በምይናማር ከ20 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች ያሉት ፌስቡክ፣ ለብዙዎች የማህበራዊ ድህረ-ገጹ ዋነኛ ወይም ብቸኛ ዜና የማግኛ ምንጭ እና የማጋሪያ መንገድ መሆኑ ይነገራል፡፡
አሁን ለቀረበበት ክስ ወዲያውኑ ምላሽ አልሰጠም የተባለው ፌስቡክ፣ በአውሮፓውያኑ 2018 በሮሂንጃ ላይ የሚደርሰውን ጥቃት እና የጥላቻ ንግግር ለመከላከል በቂ ስራ እንዳልሰራ አምኗል።