አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ኅዳር 20፣ 2014 ― የሶማሌ ክልል ርእሰ መስተዳደር የሆኑት አቶ ሙስጠፋ መሐመድ ባለፉት ቀናት ወደ ሶማሊላንድ አቅንተው ያደረጉትን ቆይታ ተከትሎ በብሔራዊ ቴሌቪዥን የተላለፈው ዘገባ ቅሬታ አስነስቷል፡፡
ርእሰ መስተዳደሩ አቶ ሙስጠፋ መሐመድ በሶማሊላንድ በነበራቸው ቆይታ ከፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ ዐብዲ ጋር በጽሕፈት ቤታቸው ቆይታ ማድረጋቸው ተገልጧል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ኢቲቪ ቆይታቸውን በተመለከተ ባሰናዳው ዘገባ የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ ዐብዲ ለሶማሊ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፋ ሙሐመድ ኡመር ‹‹ሶማሊላንድ የኢትዮጵያ መንግስት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ለሚያደረገው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ያላትን ድጋፍ መግለጻቸው›› ተጠቅሷል፡፡
ብሔራዊ ቴሌቪዥኑ ለዘገባው ዋቢ ያደረገው የሶማሊ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮን ሲሆን፣ በቢሮ የፌስቡክ ገጽ ላይ ይኸው ሠፍሮ ይገኛል፡፡
ነገር ግን በተባበሩት ዐረብ ኤሜሬት የሶማሊላንድ የቀድሞ አምባሳደር የነበሩት ሐሰን ያሲን አገራቸው የተገለጸውን አቋም እንዳላንጸባረቀች ያመለከቱ ሲሆን፣ በአንጻሩ በኢትዮጵያ ያለውን ግጭት የእርስ በርስ መሆኑንና ሁለቱም አካላት ለመፍትሔ እንዲሰሩ የአገራቸው ፍላጎት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
አምባሳደር ሐሰን ያሲን አያይዘውም የሶማሊላንድ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የንግድ ትስስርን ይበልጥ ማጠናከር እና የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠርን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን መግለጹን አስፍረዋል፡፡
ይኸው የንግድ ትስስር ማጠናከር ጉዳይ በተመሳሳይ በሶማሌ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ መረጃ ላይ ተካቷል፡፡ ከዚሁ ጋር በተገናኘ የበርበራ ወደብ በተባበሩት አረብ ኢምሬት አስፈላጊው የማስፋፊያ ግንባታ ከተደረገለት ወዲህ ለጎረቤት ኢትዮጵያ የተቀላጠፈ አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑ መነሳቱም ነው የተገለጸው፡፡
ሆኖም ርእሰ መስተዳደሩ አቶ ሙስጠፋ መሐመድ ከፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ ዐብዲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ስለ ሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተናግረውታል የተባለውን ጉዳይ በተመለከተ ከአምባሳደሩ ቅሬታ ቢሰነዘርም ከሶማሌ ኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ሆነ ጽሕፈት ቤቱን ዋቢ አድርጎ ዘገባ በሠራው ብሔራዊ ቴሌቪዥን የተሰጠ ማስተባበያ የለም፡፡