Sunday, September 22, 2024
spot_img

የአሜሪካው የአፍሪካ ቀንድ ልዑክ የአገራቸው መንግሥት ለሕወሓት ይወግናል መባሉን አስተባበሉ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ኅዳር 15፣ 2014 ― ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ድረስ በኢትዮጵያ የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀው ወደ አሜሪካ የተመለሱት የአሜሪካው የአፍሪካ ቀንድ ልዑክ ጄፍሪ ፌልትማን፣ የአገራቸው መንግሥት ለሕወሓት ይወግናል መባሉን ሐሰት ነው ሲሉ አስተባብለዋል፡፡

ፌልትማን አገራቸው ተመልሰው ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ አሜሪካ ሕወሓትን ትደግፋለች በሚል ሐሜታዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ ሆኖም ሐሰት ነው ብለውታል፡፡

ልዩ መልእክተኛው በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከሕወሓት መሪዎች ጋር መገናኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር በተገናኙበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይ አሜሪካ የፌዴራል መንግስት በሰኔ ወር 2013 መገባደጃ የተናጠል ተኩስ አቁም አድርጎ ከትግራይ መውጣቱን እንዲሁም በሰሜን እዝ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት በተመለከተ በአግባቡ እውቅና አልሰጣችሁንም በሚል ቅሬታቸውን መግለጻቸውን አመልክተዋል፡፡

ከዚሁ ጋር በተገናኘ በተደጋጋሚ አገራቸው አሜሪካ የሕወሓትን ወደ ሥልጣን መመለስ ትናፍቃለች የሚል ትርክት መኖሩን የጠቀሱት ፌልትማን፣ እንደዚህ መባሉን ተቃውመው አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡

በሌላ በኩል በዚሁ መግለጫ ወቅት የሕወሓት ኃይሎች በ1983 የኮለኔል መንግስቱ ኃይለማርያም አገዛዝ መውደቁን ተከትሎ ወደ አዲስ አበባ እንዳደረጉት ሁሉ አሁን በተመሳሳይ አዲስ አበባ ለመገስገስ ከሞከሩ ከፍተኛ የጥላቻ ምላሽ እንደሚያስተናግዱ ገልጸዋል፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ እንደ 1983 እንዳልሆነ ያስታወሱት ፌልትማን፣ ይህን የሕወሓት ሰዎች ይረዱታል የሚል እምነት እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡

በመግለጫቸው አሁንም ቢሆን ለግጭቱ ወታደራዊ መፍትሔ እንደሌለው ያነሱት ልዩ መልእክተኛው፣ በኢትዮጵያ ቆይታቸው አገኘኋቸው ያሏቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዋንኛ ፍላጎት የሕወሓት ኃይሎች በወረራ የያዟቸው የአማራ እና አፋር አከባቢዎችን ለቀው እንዲወጡ መሆኑን እንደነገሯቸው ገልጸዋል፡፡ በአንጻሩ የሕወሓት መሪዎች ቀዳሚ አላማ ከሐምሌ ወር 2013 ወዲህ ተቋርጧል ያሉትን የሰብአዊ አቅርቦት ማስከፈት መሆኑን ነግረውኛል ብለዋል፡፡

የሁለቱም አካላት አላማ ፖለቲካዊ ፍላጎት ካለ ሊሳካ እንደሚችል የገለጹ ቢሆንም፣ የፌዴራል መንግስትም ሆነ ሕወሓት ወታደራዊ አመራጮችን መቀጠላቸውን አስረድተዋል፡፡ ፌልትማን በተደጋጋሚ ወታደራዊ ግጭት መፍትሔ እንደማይሆን ወትውተዋል፡፡

አንድ ዓመት የተሻገረው የፌዴራል መንግስት እና የሕወሓት ኃይሎች ጦርነት በቅርብ ቀናት ተባብሶ መቀጠሉ የሚነገር ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መከላከያን ከውጊያ ሜዳ ለመምራት ከትላንት ጀምሮ እንደሚዘምቱ መግለጻቸው ይታወቃል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img