አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ኅዳር 8፣ 2014 ― በኦሮሚያ ክልል በሰዎች እና ተሽከርካሪዎች ላይ ተጥሎ የነበረው የምሽት እንቅስቃሴ ገደብ ለጊዜው መነሳቱን የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ወይዘሮ አዱኛ አሕመድ አስታውቀዋል፡፡
የክልሉ መንግስት ከኅዳር 3፣ 2014 ጀምሮ ከምሽት 3 ሰዓት እስከ ንጋት 11:30 ሰዎች እና ተሽከርካሪዎች እንዳይንቀሳቀሱ የሚያደርግ አዋጅ ተግባራዊ ማድረጉ ይታወቃል፡፡
እስካሁን ባለው እንቅስቃሴ የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ያነሱት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጓ፣ የክልሉን እና አገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዳይጎዳ ከግምት በማስገባት ይህ ውሳኔ መተላለፉን የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ወይዘሮ አዱኛ አሕመድ መናገራቸውን ኢቢሲ ዘግቧል፡፡
ወይዘሮ አዱኛ በቀጣይ ሁኔታዎች እየታዩ አዋጁ እንደገና በመላው ክልሉ እንዲሁም እንደየ አከባቢዎች ሁኔታ ሊታይ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
የእንቅስቃሴ ገደቡ ለጊዜው ቢነሳም፣ አስፈላጊው ፍተሻ በተለያዩ የፀጥታ አካላት እና ሕዝባዊ አደረጃጀት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አንስተዋል።