Sunday, October 6, 2024
spot_img

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ልዩ ኃይል አዛዥ እና ሁለት ባለሥልጣናት በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተሰማ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ኅዳር 7፣ 2014 ― የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ልዩ ኃይል አዛዥ ኮማንደር ኤዶሳ ጎሹን ጨምሮ፣ የግልገል በለስ ከተማ ከንቲባ አቶ ሀብታሙ ባልዳ እና የመተከል ዞን ኮሙዩኒኬሽን መምርያ ኃላፊ አቶ ገበየሁ ጀጎዴ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተሰምቷል፡፡

የክልሉ ፖሊስ ወንጀል መከላከል ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ምሥጋናው ኢንጅፋታ፣ የልዩ ኃይል አዛዡ ከሳምንት በፊት ጥቅምት 30፣ 2014 በክልሉ በሚገኘው ካማሺ ዞን በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ ነግረውኛል ሲል ሪፖርተር ጋዜጣ አስነብቧል፡፡ የግልገል በለስ ከተማ ከንቲባና የመተከል ዞን ኮሙዩኒኬሽን መምርያ ኃላፊ ደግሞ መተከል ዞን ውስጥ በተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ውሳኔ እንደታሰሩ ገልጸዋል፡፡

የእስራቸውን ሁኔታ በተመለከተ ‹‹ያልተጣሩ መረጃዎች አሉ›› ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ ያሉትን መረጃዎች እየገመገሙ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

አሁን በቁጥጥር ሥር የዋሉት ኮማንደር ኤዶሳ ጎሹ ከመስከረም 2012 ጀምሮ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ልዩ ኃይልን በአዛዥነት ሲመሩ የነበሩ መሆናቸው ታውቋል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሥር የሚገኙት መተከልና ካማሺ ዞኖች፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተደጋጋሚ በንጹሐን ላይ በሚደርስ ጥቃትና ግድያ ሥ፣ቸው ይነሳል፡፡

የመተከል ዞን በኮማንድ ፖስት ሥር የሚተዳደር ሲሆን፣ በዞኑ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ አማራ፣ ጋምቤላ፣ ደቡብና ሲዳማ ክልሎች ልዩ ኃይሎች ተሰማርተዋል፡፡ የመከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስና የአካባቢው ሚሊሻዎችም የዞኑ የፀጥታ ኃይል አካል ናቸው፡፡

የክልሉ አስተዳደር ንፁኃን ላይ ጥቃት፣ ግድያና ዕገታ እያደረሱ ያሉት የጉሙዝ ታጣቂዎች መሆናቸውን የሚገልጽ ሲሆን፣ ታጣቂዎቹ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት በተፈረጀው ሕወሓት ድጋፍ ይደረግላቸዋል የሚል ክስ ያቀርባል፡፡

ከቀናት በፊትም የመከላከያ ሠራዊትና የተለያዩ የፀጥታ አካላት ባካሄዱት ኦፕሬሽን፣ ለግልና ለቡድን ለጥቃት የሚያገለግሉ መሣሪያዎች በክልሉ በሚገኘው ሸርቆሌ ወረዳ በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ ተነግሯል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img