Sunday, September 22, 2024
spot_img

‹ኦነግ ሸኔ›› በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ቦታዎች የሚሠነዝረው ጥቃት እየተባባሰ ነው ተባለ

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ኅዳር 4፣ 2014 ― በመንግስት ኦነግ ሸኔ የሚባለውና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር የሚለው ቡድን፣ በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ እና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች በንጹኃን ሰዎች ላይ የሚሠነዝረው ጥቃት ከሰሞኑ እየተባባሰ መምጣቱ ተነግሯል፡፡

አዲስ ማለዳ ጋዜጣ ነዋሪዎችን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ የኦነግ ሸኔ ታጣቂ ኃይል በንጹሐን ዜጎች ላይ የሚያደርሰው ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃት እየተባባሰ በመምጣቱ፣ በተለይም በአምስት ወረዳዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ዙሪያ ገባውን እንደታገቱና በርካታ ሰዎች ጥቃት እየተሠነዘረባቸው ነው፡፡

ነዋሪዎቹ በአምስቱም ወረዳዎች ማለትም በጊዳ አያና፣ አቢ ደንጎሮ፣ ጉደያ ቢላ፣ ሐሮ ሊሞ እንዲሁም ትሪ በተሰኙት ወረዳዎች የሚገኙ ነዋሪዎች፣ “ሙሉ ለሙሉ ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ተከታታይ ጥቃት” እየተፈጸመባቸው ነው ብለዋል።

ጥቃቱ እየተሠነዘረብን ነው የሚሉት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ እየተባባሰ የመጣው የኦነግ ሸኔ ጥቃት ከእስካሁኑ ለየት የሚያደርገው አንዳንድ የኦሮሚያ ክልል ተወላጆች ላይም ያነጣጠረ መሆኑ ነው ሲሉ አመላክተዋል። ‹‹የአካባቢው ነዋሪዎች ቤት ንብረታቸውን ማጣት ሳይሆን የሚያሳስባቸው ሕይወታቸውን የሚያተረፉበት መንገድ አለማግኘታቸው ነው›› የሚሉት ነዋሪዎቹ፣ ታጣቂ ኃይሉ ከሚሠነዝረው ጥቃት ለማምለጥ ቢሞክሩም እንዳይወጡ በየአቅጣጫው ያሉ መንገዶች ‹‹ሆን ተብሎ›› ተዘግተውባቸዋል፡፡

አሁን ያለው ትልቁ ችግር የመንገድ መዘጋት መሆኑን የጠቆሙት ነዋሪዎቹ፣ የሚመለከተው አካል መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። ሕይወታቸውን ለማትረፍ ወደ ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ለመሸሽ ሙከራ ያደረጉ ሰዎች እንደታገቱ የተመላከተ ሲሆን፣ ለአብነትም ባሳለፍነው ሳምንት በሦስት የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ተሳፍረው ሠላም ወዳለበት አካባቢ ሲጓዙ የነበሩ ሰዎችን “ታጣቂ ቡድኑ” እንዳገታቸውና ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ አድራሻቸው እንዳልታወቀ ተገልጿል።

በዛሬው እለት መግለጫ የሰጡት የመንግስት ኮሚኒኬሽን ኃላፊ ዶክተር ለገሠ ቱሉ፣ በኦሮሚያ በአንዳንድ አካባቢዎች የሸኔ እንቅስቃሴ ነበር፣ ሆኖም በምስራቅ ወለጋ ሰሜን ሸዋ ምዕራብ ወለጋ የሸኔን እንቅስቅሴ ለማጥራት በተወሰደ እርምጃ የቡድኑን አከርካሪ መምታት ተችሏል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img