Friday, November 22, 2024
spot_img

ሳዑዲ ዐረቢያ በኢትዮጵያ ተፋላሚ አካላት ጦርነቱን እንዲያቆሙ ጠየቀች

 

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ኅዳር 4፣ 2014 ― ሳዑዲ ዐረቢያ በኢትዮጵያ ተፋላሚ አካላት ጦርነቱን እንዲያቆሙ ጠይቃለች፡፡ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትላንት ምሽት ባወጣው መግለጫ ይህንኑ አስታውቋል፡፡

ሳዑዲ በኢትዮጵያ እየተካሄደ የሚገኘውን ጦርነትና አጠቃላይ አዳዲስ ሁኔታዎችን እየተከታተለች መሆኑን የገለጸው የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ፣ አሁን ያለውን ሁኔታ ማጋጋል እንደማያስፈልግም ጠቁሟል፡፡ አገሪቱ ንጹሃን ዜጎች ላይ እንዳይደርስ እንዲሁም የረድኤት ድርጅቶች ሥራ እንዳይታወክም ሲል ጠይቋል፡፡

አሁን የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተፋላሚ አካላት ጦርነቱን እንዲያቆሙ የጠየቀችው ሳዑዲ ዐረቢያ፣ ከቀናት በፊት ዜጎቿ ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ አሳስባ ነበር፡፡

በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል የሚካሄደው አንድ ዓመት የተሻገረውን ጦርነት በሽምግልና ለመፍታት ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡

ኦባሳንጆ እያካሄዱት ባለው የሽምግልና እንቅስቃሴ የፌዴራል መንግስት እና የሕወሓት አመራሮችን አግኝተው ያናገሩ ሲሆን፣ የሁለቱም አካላት መሪዎች አሉታዊ ምላሽ እንዳልሰጧቸው ገልጸው ነበር፡፡

ሐሙስ ኅዳር 2፣ 2014 መግለጫ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ ጦርነቱን በሰላም ለመፍታት ከተፈለገ በመንግስት በኩል የሕወሓት ኃይሎች ጥቃት እንዲያቆሙ፣ ከአማራ እና አፋር ክልሎች እንዲወጡ እንዲሁም የፌደራል መንግስቱን ህጋዊነት እንዲቀበሉ ቅድመ ሁኔታ መቀመጡን ገልጸዋል፡፡ ሆኖም እንቅስቃሴዎች ቢኖሩም ወደ ድርድር አልገባንም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ነገር ግን ሕወሓት ለዚህ የአምባሳደር ዲና መግለጫ የሰጠው ምላሽ የለም፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img