Saturday, November 23, 2024
spot_img

የሱዳኑ ጦር አዛዥ ራሳቸውን የአዲሱ የአገሪቱ ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት መሪ አድርገው ሾሙ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ኅዳር 3 2014 ― በሱዳን መፈንቅለ መንግስት ያደረጉት የጦር አዛዡ ሌተናል ጀነራል አል ቡርሃን፣ አዲስ ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት አቋቁመው ራሳቸውን ሾመዋል፡፡

የጦሩ አዛዥ አል ቡርሃን የምክር ቤቱ መሪ ሆነው ቃለ መሃላ ሲፈጽሙ፣ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መሪው ጄነራል መሃመድ ሃምዳን ዳገሎ (ሄሚቴ)ን 15 አባላት ያሉት የአዲሱ ምክር ቤት ምክትል መሪ ሆነው እንደሚያስቀጥሉ ገልጸዋል፡፡

አል ቡርሃን ባቋቋሙት ምክር ቤት፣ ከ15ቱ አባላት መካከል አምስቱን ከሃገሪቱ ጦር መሪ ጄነራሎች መርጠዋል፡፡

የጦር መሪው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብደላ ሐምዶክ ይመራ የነበረውን የሲቪል መንግስት መፈንቅለ መንግስት አድርገው ያስወገዱት ከ20 ቀናት በፊት ነበር፡፡ ከሥልጣናቸው የተወገዱት ሐምዶክ በቤት ውስጥ በቁም እስር ላይ እንዳሉ ሲነገር ነበር፡፡

አል ቡርሃን መፈንቅለ መንግስቱን ሲያደርጉ ያነሷቸው ሐምዶክ፣ አዲስ የሚመሠረተውን መንግሥት ለመምራት መስማማታቸው ተነግሮ የነበረ ቢሆንም አሁንም ድረስ አዲስ ሚና ይሰጣቸው ወይም አይሰጣቸው የተገለጸ ነገር የለም፡፡

መፈንቅለ መንግስቱን ያደረጉት አል ቡርሃን፣ የሲቪል አስተዳደሩን በማስወገዳቸው ከተለያዩ አካላት ውግዘት ሲያስተናግዱ ቆይተዋል፡፡ የአፍሪካ ህብረት አገሪቱን ከአባልነት ሲያግድ፣ አሜሪካ የምትሰጠውን እርዳታ ከልክላለች፡፡ ነገር ግን የእርዳታ ክልከላውን ያደረገችው አሜሪካ አል ቡርሃን የአገራቸው አዲስ መንግስት ምስረታ እንዲያፋጥኑ ፍላጎቷ መሆኑን የሚያመለክቱ መረጃዎች ወጥተው ነበር፡፡

በሱዳን የተካሄደውን መፈንቅለ መንግስት ተከትሎ የሲቪል አስተዳድሩ ወደ ቀድሞ ስልጣኑ እንዲመለስ ሱዳናውያን በሰላማዊ ሰልፍ በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img