Tuesday, November 26, 2024
spot_img

የሱዳን ጦር አዛዥ ከሽግግር በኋላ በሚመሰረተው መንግስት ውስጥ አልሳተፍም አሉ

የሱዳን ጦር አዛዥ ሌተናንት ጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሀን ከሽግግር በኋላ በሱዳን በሚመሰረተው አዲስ መንግስት ውስጥ ተሳተፎ እንደማይኖራቸው ተናግረዋል፡፡

ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ቆይታ ያደረጉት ሌተናንት ጀነራል አብዱል ፈታህ አልቡርሀን፤ በሱዳን ዴሞክራሲያዊ የሆነ ሽግግር ለማድረግ እና ምርጫ ለማካሄድ ለራሳቸው፣ ለሱዳን ህዝብ እና ለዓለምቀፉ ማህበረሰብ ቃል መግባታቸውን አስታውቀዋል።

“ስልጣን ወደ ሲቪል አስተዳደር ለማስተላለፍ ቁርተኛ ነን” ያሉት ሌተናንት ጀነራል አልቡርሀን፤ ‹‹ሽግግሩን ሊያደናቅፍ ከሚችል ከማንኛውም ጣልቃ ገብነት ለመጠበቅ ቃል እንገባለን›› ሲሉም ተናግረዋል።

ሌተናንት ጀነራል አብዱል ፈታህ አልቡርሀን አክለውም፤ ከስልጣን የተነሱትን ዐብደላ ሐምዶክን ጨምሮ ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች ያካተተ ምክክር እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል።

በቀጣይ 24 ሰዓታት ውስጥ አዲስ መንግስት ለመመስረት የሚያስችል ስምምነት ላይ ይደረሳል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉም መናገራቸውን የአል ዐይን ዘገባ አመልክቷል፡፡

የሌተናንት ጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሀን ቃለ መጠየቅ የተላለፈው በርካታ ሱዳናውያን ለተቃውሞ አደባባይ ወጥተው ተቃውሞዋቸውን በሚያሰሙበት ወቅት መሆኑም ነው የተነገረው፡፡

አልቡርሃን ከዚሁ ጋር በተያያዘም ለተቃዎሞ አደባባይ ወጥተው ህይወታቸው ላለፈ ሰዎች የሱዳን ጦር ኃላፊነት እንደማይወስድ አስታውቀዋል።

‹‹የሱዳን ጦር ንጹሃን ዜጎችን አልገደለም›› ያሉት አልቡርሃን፤ ‹‹አሁን በጉዳዩ ላይ ምርመራ እየተካሄደ ነው፤ ከምርመራው በኋላ ምን እንደተፈጠረ የምናይ ይሆናል›› ብለዋል።

ገለልተኛ የሆነ የሱዳን ዶክተሮች ኮሚቴ ባወጣው መረጃ ከሆነ በሱዳን የተቃውሞ ሰልፎች ላይ ቢያንስ 14 ሰዎች መሞታቸውን እና ከ300 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን አስታውቀዋል።

የተቃውሞ ሰልፎቹ ከትላንት ጀምሮም የቀጠሉ ሲሆን፤ በርካታ መምህራን በካርቱም በሚገኘው የትምህርት ሚኒስቴር ህንጻ ፊት የተቃውሞ ሰልፍ ማድረጋቸውም ተነግሯል።

ሱዳን የመምህራን ማህበር ባወጣው መረጃም በትናትናው ሰልፍ ላይ ቢያንስ 80 መምህራን መታሰራቸውን አስታውቋል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img