የተባበሩት መንግሥታት ጸጥታው ምክር ቤት በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ የሚገኘው ጦርነት እየተባባሰ መሄዱ በጽኑ እንዳሳሰበውና በአስቸኳይ እንዲቆም ጥሪ አቅርቧል፡፡
ትላንት ዐርብ ጥቅምት 26፣ 2014 ምሽት ከተካሄደው የምክር ቤቱ ስብሰባ በኋላ በአስራ አምስቱም አባላቱ ተቀባይነት አግኝቶ በወጣው መግለጫ ላይ፣ ሁሉም በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት ጦርነቱን በማቆም ዘላቂ ሰላም የሚያመጣ የተኩስ አቁም ለማድረግ ውይይት እንዲጀምሩ ጥሪ ቀርቧል፡፡
የምክር ቤቱ መግለጫ ለተፈጠረው ቀውስ መፍትሔ ለማግኘት እንዲቻል እና ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ውይይት ለማካሄድ አመቺ ሁኔታ እንዲፈጠር በመጠየቅ፣ ችግሩን ለመፍታት የአፍሪካ ኅብረትን በመሰሉ አካባቢያዊ ድርጅቶች በኩል የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፉና የኅብረቱ ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ተኩስ እንዲቆምና ጦርነቱ ሰለማዊ መቋጫ እንዲያገኝ የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚደግፍ ገልጿል።
አክሎም ሁሉም ወገኖች ‹‹ከአደገኛ ጥላቻ ከሚያስፋፉ፣ ግጭትንና መከፋፈልን ከሚያነሳሱ ንግግሮች›› እንዲቆጠቡ አሳስቧል።
የመንግስታቱ ድርጅት ጸጥታው ምክር ቤት አንድ ዓመት የሞላው በትግራይ ተጀምሮ በአፋር እና አማራ ክልሎች የተስፋፋው ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ ለአስራ አንድ ጊዜያት በጉዳዩ ላይ ተወያይቷል፡፡