አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ጥቅምት 26፣ 2014 ― የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሠራጩ አደገኛ ትርክቶች ኢትዮጵያን ወደ እርስ በርስ ግጭት እንዳይከታት ስጋት አለኝ ሲሉ በትላንትናው እለት ባወጡት መግለጫ ላይ አስፍረዋል፡፡
የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመግለጫቸው፣ ከዚህ ቀደም ባወጧቸው መግለጫዎች እንደሚሉት ሁሉ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተፋላሚ አካላት በአስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
ለዚህም መንግስት ወደ ትግራይ ክልል የሚያደርገውን የአየር ጥቃቱን ጨምሮ ወታደራዊ ዘምቻውን እንዲያቆም እንዲሁም በብሔር የተደራጁ ሚሊሺያዎችን ማዝመቱን እንዲገታ ጥሪ ሲያቀርቡ፣ ለሕወሓት ኃይሎች የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ካሉት ቡድን ጋር ወደ አዲስ አበባ ‹‹የምታደርጉት ግስጋሴ አቁሙ›› የሚል መልእከት ሰደዋል፡፡ ኤርትራን አስመልክቶም ከዚህ ቀደም እንደሚሉት ሁሉ ወታደሮቿን ከኢትዮጵያ መሬት እንድታስወጣ አሳስበዋል፡፡
ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጋር በተገናኘ ተደጋጋሚ መግለጫዎችን የምታወጣው አሜሪካ፣ ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ላይ ሁለት ማእቀቦችን የጣለች ሲሆን፣ የምሥራቅ አፍሪካ ልዩ መልእክተኛዋ ጄፍሪ ፌልትማንም ለሁለት ቀናት ለሚቆይ የሥራ ጉብኝት ትላንት አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡
ፌልትማን አዲ አበባ ሲገቡ፣ በወቅታዊ የኢትዮጵያ እና ሱዳን ጉዳይ ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፈቂ መሕመት ጋር ተወያይተዋል፡፡