Monday, September 23, 2024
spot_img

በአማራ ክልል ባለው ጦርነት ሰበብ ከ6 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ለርሐብ ተጋልጧል ተባለ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ጥቅምት 25 2014 ― በአማራ ክልል በሚደረገው ጦርነት ምክንያት ከ6 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ለርሐብ መጋለጡን የክልሉ አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትና እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዘለዓለም ልጃለም ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ጦርነት በሚደረግበት በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዝቋላና ጋዝጊብላ ወረዳዎች ብቻ በምግብ፣ በመጠጥ ውሀና በመድኃኒት እጥረት 13 ሰዎች ሞተዋል።

ይህንኑ የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መልካሙ ደስታ የአስዳደሩ ነዋሪዎች በከፋ የሰብአዊ ቀውስ ውስጥ እንደሚገኙ ነግረውኛል ብሎ ዶይቸ ቬለ ዘግቧል፡፡

አቶ ዘላለም «ጠላት» ያሉት ሕወሓት ሰሜን ወሎ መቄት ወረዳን በያዘበት ወቅት 90 ሰዎችና 13 ወላዶች በመድኃኒትና በሌሎች ግብዓቶች እጥረት ሕይወታቸው እንዳለፈ ገልፀዋል፡፡ ጦርነቱን በመሸሽ ከቤት ንብረቱ የሚፈናቀለው ሰው ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን የጠቀሱት ኮሚሽነሩ፣ የተፈናቃዩ ቁጥር ከአንድ ሚሊዮን መብልጡን አስታውቀዋል።

ኮሚሽነሩ እንደሚሉት የአንዳድ አካባቢ ነዋሪዎች እስከ 4 ጊዜ ለመፈናቀል ተገድደዋል።

ኃላፊው አያይዘውም በኢትዮጵያ የሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ፣ የዓለም የህፃናት መርጃ ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት፣ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ፣ ዓለም አቀፍ ቀይመስቀል ማህበር እና ሌሎችም ዓለምአቀፍ ረጂ ድርጅቶች በጦርነት ቀጠና ላሉ ወገኖች እርዳታ ለማቅረብ ከክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶችን ያደረጉ ቢሆንም፣ እስካሁን ግን ለሕዝቡ ርዳታ አለመስጠታቸውን አስታውቀዋል።

አስቸኳይ ርዳታ የሚሻው 6 ሚሊዮን ሕዝብ እርዳታ ባለማግኘቱ ሕብረተሰቡ ከተጋረጠበት አደጋ በራሱ ትግል ሊወጣ እንደሚገባ ኮሚሽነር ዘላለም መምከራቸው ነው የተነገረው፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት በትግራይ ክልል ተቀስቅሶ ካለፈው ዓመት ሰኔ ወር መገባደጃ ወዲህ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች የተስፋፋው የፌዴራል መንግስት እና የሕወሃት ኃይሎች ጦርነት ከሰሞኑ ተባብሶ መቀጠሉ ይነገራል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img