አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ጥቅምት 24፣ 2014 ― ከአንድ ዓመት በፊት የሕወሓት ኃይሎች በሰሜን ዕዝ ላይ ፈጽመውታል የተባለውን ጥቃት የሚዘክር መሰናዶ በተለያዩ የመንግስት ተቋማት ተካሄዷል።
በዛሬው እለት በአዲስ አበባ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ጽሕፈት ቤት በዋናነት በተዘጋጀው ሥነ ሥርዓት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የመከላከያ ኤታማጆር ሹሙ ብርሃኑ ጁላ እና የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ ተገኝተዋል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ ከአንድ ዓመት በፊት በህወሓት ኃይሎች በፈጸመባቸው ጥቃት ሕይወታቸው ላለፈ የአገሪቱ ሠራዊት አባላትን ለማሰብ የህሊና ጸሎት እና የሻማ ማብራት መርሃ ግብር ተደርጓል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የዛሬውን መታሰቢያ አስመልክቶ ባሰራጩት ማስታወሻ ጥቅምት 24፣ 2013 በግፍ የተገደሉት የአገሪቱ ወታደሮች ብቻ ሳይሆኑ ኢትዮጵያም ጭምር ናት ብለዋል።
አምና ጥቅምት 24 ግፍ የተፈጸመባቸው ጀግኖቻችን ታሪክ ፈጽሞ የሚረሳ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ዛሬ የቆምነው ለእኛ ሲሉ የግፍ ጽዋን በተጎነጩ ጀግኖቻችን አጥንት ላይ ነው። እነዚያ ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጆች “ከወገኔ በፊት እኔ ልቅደም” ብለው ደማቸውን ለአፈር፣ ሥጋቸውን ለአሞራ ባይሰጡ ኖሮ የዛሬው ቀን ዛሬን ባልመሰለ ነበር ብለዋል።
አያይዘውም የሽብር ያሉት ቡድን፣ በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመው ጥቃት መሣሪያ ለመዝረፍ ብቻ የተደረገ ተራ ጥቃት አልነበረም ሲሆን፣ በተንኮል የተቀመመና በክፋት የሞላ መሆኑ የተለየ ያደርገዋል ሲሉም አክለዋል።
በሌላ በኩል ዛሬ ሽብር ቡድኑ የተሰጠውን የጥሞና ጊዜ እንድ እድል ከመጠቀም ይልቅ እንደ ድል ወስዷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ “በአማራና በአፋር ክልል በሚኖሩ ወገኖቻችን ላይ የግፍ በትሩን ቀጥሎበታል” ብለዋል።
የጥፋት አጋሩ ያሉት “ሸኔም በኦሮሚያ ክልል ወለጋ አካባቢ ልዩ ልዩ አደጋዎችን እየጣለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያንን ረፍት እየነሣ ነው” ያሉ ሲሆን፣ ሌሎችም የጥፋት ኃይሎች ከውስጥም ከውጭም ወኪሎቻቸውን አስተባብረው በሙሉ ዐቅማቸው ኢትዮጵያ ላይ መዝመታቸውን እንደገፉበት ገልፀዋል።
በማሳረጊያቸው “ሠራዊታችን ብቻውን ተጋፍጦ የድል ዜና እንዲያበስረን መጠበቅም ሞኝነት ነው” ያሉት ዐቢይ፣ “ጠላቶቻችን ተባብረው የደቀኑብን አደጋ ሁላችንም ተባብረን ካልመከትነው ድል የማይታሰብ ነው” ሲሉም አስፍረዋል።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት 24 በትግራይ የተቀሰቀሰው ጦርነት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በርካቶችን የቀጠፈ ሲሆን፣ በሚሊዮኖች ደግሞ እንዲፈናቀሉ አድርጓል።