Sunday, October 6, 2024
spot_img

ዐብደላ ሐምዶክ አሁንም በቁም እስር ላይ ናቸው ተባለ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ጥቅምት 22፣ 2014 ― ከሳምንት በፊት ከሱዳን ሽግግር መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው የተነሱት ዐብደላ ሃምዶክ አሁንም በቁም እስር ላይ መሆናቸውን ያስታወቀው ጽሕፈት ቤታቸው ነው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት የዐብደላ ሐምዶክን የቤት ውስጥ እስር በተመለከተ ዛሬ ዝርዝር መግለጫ አውጥቷል፡፡ ጽሕፈት ቤታቸው ከዐብደላ ሃምዶክ ጋር ያለኝ የመገናኘት ሁኔታ ውስን ነው ማለቱን አል ዐይን ዘግቧል፡፡

በሌላ በኩል በሱዳን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ ቮከር ፔርዝ በትላናትናው እለት በዐብደላ ሃምዶክ መኖሪያ ቤት ተገኝተው ውይይት ማድረጋቸውን የገለጹ ሲሆን፣
ለሱዳን ችግሮች የጋራ መፍትሄዎችን በጋራ እንፈልጋለን ያሉት ልዩ መልዕክተኛው፣ በቀጣይ መፍትሔዎች ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡

በሱዳን ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ የተካሄደውን የመፈንቅለ መንግሥት የመሩት ሌ/ጄነራል ዐብዱልፈታህ አል ቡርሃን በአገሪቱ በሙያተኞች የሚመራ መንግስት እንደሚመሰረት ገልጸዋል።

አል ቡርሃን አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር እና ሉዓላዊ ምክር ቤቱ በቀናት ውስጥ ቢበዛ በሳምንት ውስጥ ይፋ እንደሚደረጉም ገልጸው ነበር፡፡ ባለፉት ቀናት በወጡ መረጃዎች ከመፈንቅለ መንግስቱ ጋር ተያይዞ በጦሩ ታስረው የሚገኙት ዐብደላ ሃምዶክ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ቀዳሚው እጩ መሆናቸውን የአገሪቱ ጦር አዛዥ ሌተናል ጀነራል አል ቡርሃን ተናግረዋል።

መንግስት ሊመሰርት የሚችለው ጠቅላይ ሚኒስትር በጦሩ ስምምነት ይመረጣል ያሉት ቡርሃን፣ ተመራጩ ጠቅላይ ሚኒስትር ያለ ጦሩ ጣልቃ ገብነት መንግስት እንደሚያዋቅር ገልጸዋል፡፡

ሆኖም አሁንም በቁም እስር ላይ ናቸው የተባሉት ሐምዶክ፣ ፍላጎት ይኖራቸው አይኑራቸውም የተገለጸ ነገር የለም፡፡

በሱዳን የተካሄደውን መፈንቅለ መንግስት ተከትሎ የአፍሪካ ኅብረት የሱዳን ሲቪል አስተዳደር እስኪመለስ ድረስ አገሪቱን ማገዱ ይታወቃል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img