Sunday, October 6, 2024
spot_img

የሱዳን ጦር አዛዥ አገሪቱን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ለመምራት ሐምዶክ የመጀመሪያ እጩ ናቸው አሉ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ጥቅምት 19፣ 2014 ― በሳምንቱ መጀመሪያ በሱዳን የተካሄደውን የመፈንቅለ መንግሥት የመሩት ሌ/ጄነራል ዐብዱልፈታህ አል ቡርሃን በአገሪቱ በሙያተኞች የሚመራ መንግስት እንደሚመሰረት ገልጸዋል።

አል ቡርሃን አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር እና ሉዓላዊ ምክር ቤቱ በቀናት ውስጥ ቢበዛ በሳምንት ውስጥ ይፋ እንደሚደረጉም ገልጸዋል፡፡

አል ዐይን ዐረብኛ እንደዘገበው ከሆነ በሰሞኑ መፈንቅለ መንግስት በጦሩ ታስረው የነበሩት ዐብደላ ሃምዶክ ለጠቅላይ ሚኒስትርነቱ ቀዳሚው እጩ መሆናቸውን ቡርሃን ተናግረዋል።

ዐብደላ ሃምዶክ በቡርሃን የሚመራው ጦር የሽግግር መንግስቱን ከማፍረሱ በፊት የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር እንደነበሩ ይታወቃል፡፡

የዜና ምንጩ ሌተናል ጀነራል ዐብዱልፈታህ አል ቡርሃን አሁንም ሃምዶክ “ራሳቸውን ካልቆጠቡ በስተቀር ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ከሚታሰቡት እጩዎች ቀዳሚው ናቸው” ማለታቸው አስነብቧል።

መንግስት ሊመሰርት የሚችለው ጠቅላይ ሚኒስትር በጦሩ ስምምነት ይመረጣል ያሉት ቡርሃን፣ ተመራጩ ጠቅላይ ሚኒስትር ያለ ጦሩ ጣልቃ ገብነት መንግስት እንደሚያዋቅር ተናግረዋል፡፡

“የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በፖለቲካ እና በጦሩ ስምምነት ነበር የተመረጠው፡፡ አሁን ግን የፖለቲካ ኃይሎቹ የሉም፡፡ በመሆኑም ህዝቡን እስከ ምርጫ ድረስ የመምራት ኃላፊነት ይኖርብናል፡፡ ከተማሩት መካከልም ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንመርጣለን” ሲሉ ለሩሲያው ስፑትኒክ ጨምረው ተናግረዋል።

ሆኖም በስፑትኒክ ዘገባ እነማን ለጠቅላይ ሚኒስትርነት እጩ ሆነው እንደቀረቡና እንደሚወዳደሩ አልገለጹም፡፡

የሱዳን ጦር በሲቪል መንግሥቱ ላይ መፈንቅለ መንግሥት ማካሄዱን ተከትሎ የዓለም ባንክ ለአገሪቱ የሚሰጠውን እርዳታ አቁሟል። ከዚህ በተጨማሪም አፍሪካ ህብረት የሲቪል አስተዳደሩ ወደ ስልጣኑ እስኪመለስ ድረስ ሱዳን አግዷታል። አሜሪካ እና አሜሪካም ተመሳሳይ አቋም አንፀባርቀዋል።

በጦሩ አዛዥ አሁንም ለጠቅላይ ሚኒስትርነት እጩ ናቸው የተባለላቸው ዐብደላ ሐምዶክ ሰኞ እለት በቁጥጥር ስር ውለው ወደ አልታወቀ ሥፍራ መወሰዳቸው ተነግሮ የነበረ ቢሆንም፣ በማግስቱ አል ቡርሃን ለሚዲያ ቀርበው እኔ ቤት ይገኛሉ ማለታቸው አይዘነጋም። ከዚህ መግለጫ በኋላ ሐምዶክ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ተመልሰው በከፍተኛ ጥበቃ ስር እንደሚገኙ የተነገአ ቢሆንም፣ በመገናኛ ብዙሃን ፊት አልቀረቡም።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img