Sunday, October 6, 2024
spot_img

የዓለም ባንክ የሱዳንን እርዳታ ማቋረጡን አስታወቀ

 

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ጥቅምት 18 2014 ― የሱዳን ጦር በሲቪል መንግሥቱ ላይ መፈንቅለ መንግሥት ማካሄዱን ተከትሎ የዓለም ባንክ ለሱዳን የሚሰጠውን እርዳታ ማቆሙን አስታውቋል፡፡

በጉዳዩ ላይ የተናገሩት የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት ዴቪድ ማልፓስ በሱዳን ያሉ የቅርብ ጊዜ ክስተቶች በጣም እንደሚያሳስብ በመግለጽ፣ ክስተቱ በአገሪቱ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ የማገገም ሂደት እና እድገት ላይ ‹‹ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል ብዬ እሰጋለሁ›› ብለዋል፡፡

በሌተናል ጀነራል ዐብዱልፈታህ አልቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦር የሲቪል አስተዳደሩን መሪዎች በቁጥጥር ሥር ማዋሉ የተሰማው ሰኞ ጥቅምት 15፣ 2014 ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዐብደላ ሐምዶክን ጨምሮ ባለስልጣናቱ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ጦሩ በርካታ ተቃውሞዎችን አስተናግዷል፡፡

የአህጉሩ መሪ ድርጅት አፍሪካ ኅብረት በትላንትናው እለት አገሪቱ የሲቪል አስተዳደሩን ወደ ቦታው እስክትመልስ ድረስ ከአባልነት ያገዳት ሲሆን፣ አሜሪካ ደግሞ በእርዳታ የምትሠጠውን 700 ሚሊዮን ዶላር አልሰጥም ብላለች፡፡

ከቀናት በፊት በሱዳን የተካሄደውን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ተከትሎ፣ በ12 ሀገራት የሚገኙ የሱዳን አምባሳደሮች ድርጊቱን እንደሚቃወሙ ባወጡት የጋራ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

ይህንኑ ተከትሎ የጦር አዛዡ አል ቡርሃን የአሜሪካ እና አውሮፓ ህብረትን ጨምሮ በተለያዩ አገራት ሱዳንን የወከሉ አምባሳደሮችን አሰናብተዋል፡፡

ድርጊቱን የተቃወሙት የሱዳን አምባሳደሮች በአሜሪካ፣ ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ቤልጅየም፣ አውሮፓ ህብረት፣ ስዊዘርላንድ፣ የተመድ ኤጀንሲዎች፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኳታር፣ ኩዌት፣ ቱርክ፣ ስዊድን እና ካናዳ የሚገኙ ናቸው።

በአገሪቱ የተካሄደው መፈንቅለ መንግስት በዜጎች የጎዳና ላይ ተቃውሞ ያስተናገደ ሲሆን፣ በቀጠለው ተቃውሞ የመንግስት ወታደሮች በሕዝቡ ላይ ተኩስ ከፍተው በትንሹ 10 ሰዎች ሲገደሉ በመቶዎች መቁሰላቸውን የአልጀዚራ ዘገባ ያመለክታል፡፡ ወታደሮች በካርቱም ቤት ለቤት በመዞር የተቃውሞ አስተባባሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውም ተዘግቧል።

ከተቃውሞ አድራጊዎቹ ጋር ሐኪሞች እና የነዳጅ ሠራተኞችን የወከሉ የሠራተኛ ማኅበራት እየተቀላቀሉ ሲሆን፣ የሱዳን የባንክ ማኅበር ሠራተኞችም ተመሳሳይ እርምጃ እየወሰዱ እንደሚገኙ ተነግሯል፡፡ ቢቢሲ የማኅበሩ ቃል አቀባይ ዐብዱልረሺድ ከሊፋ ‹‹ማንኛውንም ወታደራዊ እርምጃ እና ማንኛውንም ዓይነት አምባገነንነት በፅኑ እንቃወማለን›› እንዳሉት አስነብቧል፡፡

ሱዳንን ለረዥም ዓመታት የመሩት ዑመር ሐሰን አልበሽር ከስልጣን መወገዳቸውን ተከትሎ ሥልጣን የተካፈሉት የሱዳን ሲቪል እና ወታደራዊ መሪዎች ላለፉት ሁለት ዓመታት በሥልጣን ክፍፍል ፍጥጫ ላይ እንደቆዩ ይታወቃል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img