- የሱዳን ወታደራዊ አመራር በርካታ የሲቪል መንግስት አመራሮችን እያሠረ ይገኛል
አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ጥቅምት 15፣ 2014 ― የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብደላ ሐምዶክ በወታደራዊ አመራሩ በቁም እስር እንዲቆዩ መደረጋቸው ተነግሯል፡፡ የአገሪቱ ወታደራዊ አመራር ከትላንት ሌሊት ጀምሮ እያካሄደው ነው የእስር ዘመቻ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በቁም እስር እንዲቆዩ ከማድረጉ ተጨማሪ ሲቪል አመራሮችን እየተለቀመ እንደሚገኝ አል ሀደስ የተባለው ቴሌቪዥን ዘግቧል፡፡
እንደ ቴሌቪዥኑ ዘገባ እስካሁን ድረስ በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ ኢብራሂም አል ሸይኽ፣ የማስታወቂያ ሚኒስትሩ ሐምዛ ባሉል፣ የዐብደላ ሐምዶክ የሚዲያ አማካሪ ፈይሰል መሐመድ ሳሌህ ይገኙበታል፡፡
ከነዚህ በተጨማሪም የሱዳን ሉአላዊ ምክር ቤት ቃል አቀባይ የሆኑት መሐመድ ለ ፊቂ ሱለይማን እና የካርቱም ገዢ አይመን ኻሊድ በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል ተካተዋል፡፡
ይህንኑ ተከትሎ ሱዳናውያን ወደ አገሪቱ መዲና ካርቱም አደባባዮች ለተቃውሞ መትመም የጀመሩ ሲሆን፣ የመገናኛ አገልግሎት በመቋረጡ መረጃዎች በበቂ ሁኔታ እየወጡ አለመሆኑን የአል ጀዚራ ዘገባ አመልክቷል፡፡ የዜና ተቋሙ በሪፖርቱ የሱዳን ወታደራዊ አመራር ወደ ካርቱም የሚወስዱ ሁሉንም መንገዶች መዝጋቱንም ጠቅሷል፡፡
ሱዳን በቅርቡ መፈንቅለ መንግስት ተካሄዶባት እንደከሸፈ መነገሩ አይዘነጋም፡፡ መፈንቅለ መንግስቱን ተከትሎ በሱዳን ጦር እና በሲቪል መንግስት መካከል ቅራኔ መነሳቱን የሚያመለክቱ መረጃዎች ሲወጡ ቆይተዋል፡፡ ባለፉት ቀናት በአገሪቱ መዲና ካርቱም በተለያየ ጊዜ ሁለቱንም አካላት የሚቃወሙ ሰልፎች ተስተናግደዋል፡፡