Monday, November 25, 2024
spot_img

የሱዳን ሽግግር መንግሥት ደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች በካርቱም የተለያየ ተቃውሞ አደረጉ

 

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ጥቅምት 12 2014 ― በጎረቤት አገር ሱዳን የአገሪቱን ሽግግር መንግሥት የሚደግፉ በካርቱም ጎዳናዎች ተቃውሞ ሲያካሄዱ፣ ይህንኑ የሽግግር መንግስት የሚቃወሙ ደግሞ ወታደራዊ መንግሥቱን በመደገፍ በቤት የመቀመጥ አድማ አድርገዋል።

በመስከረም ወር በአልበሽር ተከታዮች ተደረገ ከተባለው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በኋላ በወታደራዊ እና በሲቪል መሪዎች መካከል ቅራኔ ያስተናገደችው ሱዳን፣ ይኸው ከፍተኛ መከፋፈል ወደ ዴሞክራሲ የምታደርገውን ሽግግር ሊያደናቅፈው ይችላል በሚል ስጋቶች ሲነገሩባት ይደመጣል፡፡

አሁን መስማማት ያቃታቸው ሁለቱ አካላት አገሪቱን ለረዥም ጊዜ በፕሬዝዳንት ያገለገሉት ዑመር አል በሽር ከሁለት ዓመት በፊት ከስልጣን መነሳታቸውን ተከትሎ ስልጣን ለመጋራት ተስማምተው ነበር።

ትላንት ሐሙስ ዕለት የሲቪሉን መንግሥት የሚደግፉ ሰልፈኞች ጎማ ሲያቃጥሉ እና የሱዳን ባንዲራን ሲያውለብልቡ የፀጥታ ኃይሎች አስለቃሽ ጭስ ተኩሰዋል። ቤታቸው በመቀመጥ ተቃውሞ ያደረጉት የጦሩ ደጋፊዎች በበኩላቸው የሲቪል መንግሥት እንዲወገድና ጦር ሠራዊቱ ቦታውን እንዲይዝ ይፈልጋሉ። አሁን ያለውን አስተዳደር የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት እንዲነቃቃ ካለማድረጉ በተጨማሪ የዳቦ እጥረት እንዲከሰት ምክንያት ነው በማለት ይከሱታል።

ባለፋው ሳምንት ቅዳሜ ዕለት አደባባይ ወጥተው የነበሩት እነዚሁ የጦሩ ደጋፊዎች ‹‹የረሀቡ መንግሥት ይውረድ›› ሲሉ መፈክር ያሰሙ ሲሆን፣ የጦር ኃይሎች እና የሱዳን የጋራ ወታደራዊ-ሲቪል ሉዓላዊ ምክር ቤት መሪው ጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐን መፈንቅለ መንግሥት በማድረግ አገሪቱን እንዲቆጣጠሩ ጥሪ አቅርበዋል።

እነዚህን የተቃወሙት በትላንትናው እለት በካርቱም አደባባይ የወጡ ሰዎች ደግሞ ‹‹ሲቪሉ የሕዝብ ምርጫ ነው›› የሚሉ መፈክሮችን የያዙ ሲሆን፣ ከቀደሙት በተቃራኒ ‹‹አል ቡርሐን ስልጣንን ይልቀቁ›› ሲሉ እንደነበር አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል፡፡

በሱዳን ያለው ሁኔታ አሳስቦኛል ያለችው አሜሪካ፣ በውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን በኩል ሁሉም ወገኖች የተስማሙበትን ዴሞክራሲያዊ ሽግግር እንዲከተሉ ብላለች፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img