አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ጥቅምት 10፣ 2014 ― ግዙፉ የማኅበራዊ ትስስር መድረክ ፌስቡክ ሥም ለውጥ ለማድረግ ማቀዱ ተሰምቷል፡፡ ኩባንያው የሥም ለውጥ የሚያደርገው በቀጣይ ሳምንት መሆኑን ዘ ቨርጅ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት አላቸው ያላቸውን ሰዎች ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
የሥም ለውጡን በተመለከተ የኩባንያው መስራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማርክ ዙከርበርክ በቀጣይ ሳምንት በሚካሄደው ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ንግግር እንደሚያደርግ ያመለከተው ዘገባው፣ ጉዳዩ በቶሎ ይፋ እንደሚደረግም ገልጧል፡፡
ነገር ግን በጉዳዩ ላይ ኩባንያው ይፋዊ ማብራሪያ አልሰጠም፡፡ በዘገባው ላይ የኩባንያው ሰዎች ለአሉባልታዎች ምላሽ አንሰጥም ማለታቸውም ሰፍሯል፡፡
ኩባንያው የሥም ለውጡን የሚያደርገው ቀጣዩ የበይነ መረብ ዝግመተ ለውጥ ነው በሚባለው ሜታቨርስ ማስፋፊያ ጋር በተገናኘ ነው የተባለ ሲሆን፣ ኩባንያው ራሱን ከማኅበራዊ ትስስር መድረክነት የላቀ ሥፍራ እንዲኖረው ውጥን መያዙን የሚያመለክት መሆኑም ተነግሮለታል፡፡
የሥም ለውጥ ሊያደርግ መሆኑ የተነገረለት ፌስቡክ፣ በቅርብ ጊዜያት በተለይ ከሚያራምደው ፖሊሲ እና ተዛማጅ ጉዳዮች ጋር በተገናኘ የተለያዩ ትችት አዘል አስተያየቶችን ሲያስተናግድ መሰንበቱ ይታወቃል፡፡
በኩባንያው ላይ ወቀሳ ካቀረቡት መካከል የሆኑት የቀድሞ ሠራተኛው የዳታ ሳይንቲስቷ ፍራንሴስ ሃውገን በአሜሪካ ሕግ አውጭ ኮሚቴ ፊት ቀርበው ኢትዮጵያን ጨምሮ በአንዳንድ ሀገራት የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን መግታት እየቻለ አላስቆመም የሚል ውንጀላ አቅርበውበት ነበር፡፡
የቀድሞዋ የፌስቡክ ሠራተኛ ኩባንያው ይህን አካሄድ በመምረጡ በአገራቱ የበዛ መከፋፈል፣ በርካታ ውሸት እና ስጋት ማስከተሉን በመግለጽ፣ በኦንላይን ሚዲያው የሚሠራጩ አደገኛ ንግግሮች በሰዎች ላይ እስከ ሞት ማስከተላቸውንም አመልክተዋል፡፡
በተመሳሳይ ሶፊ ዣንግ የተባለች በፌስቡክ ኩባንያ ውስጥ የዳታ ሳይንቲስት ሆና ስትሰራ የቆየች ግለሰብ፣ መስርያ ቤቱ የሚሰራቸው ጥፋቶች ላይ ክስ ለማቅረብ እና ከዚህ ቀደም የነበሩበት ክሶች ላይ ለመመስከር የሚረዱ ሰነዶችን ለአሜሪካ ሕግ አስከባሪ ኤጀንሲ ማስተላለፏን ለሲኤንኤን ስትናገር ተደምጣለች፡፡
ግዙፉ የማኅበራዊ ትስስር መድረክ ፌስቡክ፣ በዓለማችን በ111 ቋንቋዎች አገልግሎት የሚሰጥ ነው፡፡