Friday, November 22, 2024
spot_img

በምሥራቅ ወለጋ ውስጥ የተፈጸመውን ጥቃት አድራሹ ኦነግ ሸኔ ሲል የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ከሰሰ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ጥቅምት 4 2014  በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ወለጋ ዞን፣ በኪረሙ ወረዳ ውስጥ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የተፈጸመውን ጥቃት አድራሹ በመንግስት ኦነግ ሸኔ የሚባለውና ራሱን የኦሮሚያ ነጻነት ሠራዊት ሲል የሚጠራው ቡድን መሆኑን የክልሉ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ገልጸዋል፡፡  

አቶ ኃይሉ ‹‹እዚያ አካባቢ ችግር የፈጠረው ከሕወሓት የወሰደውን ተልዕኮ ለማስፈጸም በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው አክራሪው ኦነግ ሸኔ ነው›› ሲሉ ቡድኑን ከስሰዋል።

በምሥራቅ ወለጋ ሀሮ በተባለ አካባቢ በተፈጸመ ጥቃት በርካታ ንጹሀን ሰዎች እንደተገደሉ፣ ከቤት ንብረታቸው እንደተፈናቀሉ እንዲሁም የንብረት ውድመትም እንደደረሰ ተነግሯል።

ባለፈው እሑድ መስከረም 30፣ 2014 ከተፈጸመ ጥቃት ጋር በተያያዘ የ15 ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን መረጃ እንዳላቸው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ነግረውኛል ብሎ ቢቢሲ አስነብቧል፡፡

በአካባቢው ቅዳሜ እኩለ ቀን ላይ ተጀምሯል ለተባለው ግጭት የተለያዩ የዜና ምንጮች ያናገራቿቸው በአማራ እና በኦሮሞ ወገን ያሉ ማኅበረሰቦች ለተፈጸመው ጥቃት እርስ በእርስ በመወነጃጀል ለደረሰው ጥቃት አንዳቸው የሌላኛቸውን ወገን ተጠያቂ ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡

በአንድ በኩል ግጭቱ የተነሳው በሁለቱም ተወላጆች ነዋሪዎች መካከል እንደሆነ ሲነገር፣ በሌላ በኩል ደግሞ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር የሚለው እና መንግሥት ሸኔ የሚለው ቡድን እንዲሁም የአማራ ሚሊሻ ከግጭቱ ጋር በተያያዘ እጃቸው አለበት የሚሉ ውንጀላዎች ተሰምተዋል፡፡

በጥቃቱ የሞቱትን ሰዎች በተመለከተ የክልሉ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ 15 ሰዎች መገደላቸውን ሲናገሩ፣ በሌላ በኩል የሟቾቹ ቁጥር ከ20 እንደሚልቅ የሚያመለክቱ መረጃዎች ወጥተዋል፡፡

ጥቃቱን እንዴት ደረሰ ከሚለው ጋር ተያይዞ አዲስ ስታንዳርድ ድረ ገጽ ይዞት በወጣው ዘገባ ምስክርነታቸውን የሰጡ የአካባቢው ሽማግሌ እንዳሉት፣ በአካባቢው የነበረው የኦሮሚያ ልዩ ኃይል አካባቢውን እንዳይለቁ ለአስተዳዳሪዎች ተናግረው የነበረ ቢሆንም፣ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ መስከረም 26፣ 2014 ልዩ ኃይሉ ሥፍራውን መልቀቁን አስታውሰው፣ ግጭቱ የተከሰተውም የልዩ ኃሉ ከወጣ ከአራት ቀናት በኋላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በጥቃቱ የበርካቶች ሕይወት እንደተቀጠፈ የገለጹት የአገር ሽማግሌ፣ ከሟቾቹ መካከል የሚበዙት የኦሮሞ ተወላጆች ናቸው ብለዋል፡፡ የአገር ሽማግሌው ይህ እንደሚሆን ቀድመው ጠርጥረው የነበረ ቢሆንም፣ ይህ ባለመደረጉ ጥፋቱን ማስከተሉንም አመልክተዋል፡፡

በሥፍራው በአሁኑ ወቅት ሰላም እየወረደ መሆኑን የተናገሩት የኦሮሚያ ክልል ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ፣ በአንዳንድ ዘገባዎች ከሌላ አካባቢ የመጣ ኃይል ጥቃት አድርሷል መባሉንም አስተባብለዋል፡፡ አያይዘው ግጭቱን የቀሰቀሱት ኃይሎች ‹‹አጀንዳቸው አማራ እና ኦሮሞን ማጋጨት ስለሆነ እነዚህ እየተናበቡ እየተንቀሳቀሱ ነው። የህወሓትን አጀንዳ ለማስፈጸም ካልሆነ በስተቀር ከሌላ አካባቢ መጥቶ እዚያ ቦታ የሚንቀሳቀስ ኃይል የለም›› ማለታቸውን የቢቢሲ ዘገባ አመልክቷል፡፡

በምሥራቅ ወለጋ ኪራሙ ወረዳ በመስከረም የመጀመሪያዉ ቀናት በተመሳሳይ በደረሰ ጥቃት 29 ንጹሐን መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ማሳወቁ አይዘነጋም፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img