አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ጥቅምት 3፣ 2014 ― በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ ከሳምንታት በፊት በኢትዮጵያ ላይ ማእቀብ ለመጣል ውሳኔ ያሳለፉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የኬንያውን አቻቸው ኡሁሩ ኬንያታን ነገ በዋሽንግተን አግኝተው ሊወያዩ መሆኑ ተሰምቷል።
ይህ የሁለቱ አገራት መሪዎች ስብሰባ ባይደን ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ከአፍሪካ መሪ ጋር የሚያደርጉት የመጀመሪያው እንደሚሆን ተነግሯል።
የኋይት ሀውስ ቃል አቀባይ ጄን ፕሳኪ በሰጡት መግለጫ ሁለቱ መሪዎች “ዲሞክራሲን እና ሰብአዊ መብቶችን ለማስጠበቅ፣ ሰላምን እና ደህንነትን ለማረጋግጥ፣ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማፋጠን እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በሚደረጉ ጥረቶች” ላይ ይወያያሉ ማለታቸውን የሬውተርስ ዘገባ ያመለክታል።
ፕሬዝዳንት ኡሁረ ኬንያቲ የሚመሯት ጎረቤት አገር ኬንያ ከቀናት በፊት በኢትዮጵያ ጉዳይ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ሁለቴ የተሰበሰውን የመንግስታቱን ድርጅት በጥቅምት ወር በፕሬዝዳንትነት እየመራች እንደምትገኝ ይታወቃል።