አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ጥቅምት 1፣ 2014 ― የቤጃ ጎሳዎች ፖርት ሱዳንን መዝጋታቸውን ተከትሎ በካርቱም የነዳጅ እና የዳቦ እጥረት ማጋጠሙን የሚያመለክቱ መረጃዎች ወጥተዋል፡፡ የሱዳን ዋነኛ የገቢ እና ወጪ ንግዶች የሚከናወኑበት ፖርት ሱዳን የቤጃ ጎሳዎች ባስነሱት ተቃውሞ ከተዘጋ ከሦስት ሳምንት በላይ ሆኖታል።
ከፖርት ሱዳን ወደ አገሪቱ ማዕከል ካርቱም እና ሌሎች ከተሞች የሚደረገው የትራንስፖርት እንቅስቃሴ አሁንም መስተጓጎሉ ሲገለጽ፣ በዚሁ ምክንያት በካርቱም የስንዴ ዱቄት እና ነዳጅ እጥረት ማጋጠሙን ሬውተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል፡፡
እጥረቱ ወትሮም ቢሆን በሀይል እጥረት ውስጥ ላለችው ሱዳን ተጨማሪ ችግሮችን እየፈጠረ መሆኑን የገለጸው ዘገባው፣ ችግሩን ለመፍታት በአገሪቱ መንግስት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆናቸውም ነው የተገለጸው፡፡
የሱዳን የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ካሊድ ኦማር የሱፍ በበኩላቸው በሱዳን ያጋጠመውን የስንዴ ዱቄት እና የነዳጅ እጥረት ለመፍታት መንግስት ከመጠባበቂያ ክምችቶች በመውጣት እንደሚያከፋፍል ለዜና ወኪሉ ተናግረዋል።
ባሳለፍነው አርብ አሜሪካ፤ እንግሊዝ እና ኖርዌይ የሱዳን የሲቪል አስተዳደር አመራሮች የፖለቲካ ውይይት በማድረግ በአገሪቱ የተፈጠሩ ውጥረቶችን እንዲያረግቡ አሳስቦ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
በምስራቅ ሱዳን የሚገኙት እነዚሁ የጎሳ አባላት ፍትሃዊ ውክልና እና ተጠቃሚነት የማይኖር ከሆነ የአገሪቱ አካል ሆነው መቀጠል እንደማይፈልጉ ማስታወቃቸው አይዘነጋም፡፡
ይህንኑ ተከትሎ ባስነሱት ተቃውሞ ከተዘጉ ቦታዎች መካከል ወደ ፖርት ሱዳንና ሱዋኪን ወደቦች የሚወስደው መንገድ በሬድሲ ግዛት አቃባን ጨምሮ፣ ከግብጽ ጋር የሚያገናኘው ኦሲፍ መንገድም ይገኝበታል፡፡
ከቀናት በፊት የፖርት ሱዳን ወደብ መዘጋቱን ይፋ ያደረገው የአገሪቱ ካቢኔ፣ ተቃውሞ አድራጊዎቹ ተቃውሟቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲያሰሙ በመጠየቅ፣ አሁን እየወሰዱ የሚገኘው እርምጃ የመላው ሱዳንያውያንን ጥቅም የሚጎዳ ነው ብሎ ነበር፡፡
ለተፈጠረው ችግር ፖለቲካዊ መፍትሔ እንደሚፈልግለት ያሳወቀው ካቢኔው፣ ተቃውሞ አድራጊዎቹ ከመንግስት ጋር ለንግግር እንዲቀመጡም ጥሪ ማቅረቡ መነገሩ አይዘነጋም፡፡