Saturday, November 23, 2024
spot_img

የታሊባን እና የአሜሪካ ባለሥልጣናት በዶሃ የፊት ለፊት ውይይት አደረጉ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ጥቅምት 1 2014 ― ታሊባን ባለፈው ነሐሴ 9፣ 2013 ካቡልን ከተቆጣጠረ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር በኳታር ዶሃ ውይይት አካሄዷል፡፡

በኳታር የተደረገው ውይይት ዋነኛ አንኳር ሐሳቦች በደህንነት ጉዳዮች፣ በአክራሪነት ዙሪያ እና የሴቶችን ተሳትፎ በተመለከተ እንደነበር ተነግሯል፡፡

አሜሪካ ውይይቱን በተመለከተ ለታሊባን እውቅና የሚሰጥ አይደለም ያለች ቢሆንም፣ ታሊባን ትላንት አመሻሹን በለቀቀው መረጃ አሜሪካ ሰብዓዊ እርዳታ ለአፍጋኒስታን ለማቅረብ መስማማቷን ገልጿል።

ታሊባን በመግለጫው፣ ‹‹የዩኤስ ተወካዮች እንዳሉት ለአፍጋናውያን የሰብዓዊ እርዳታ ያቀርባሉ፤ ለሌሎች የዕርዳታ ድርጅቶች ደግሞ ድጋፍ ያደርጋሉ›› ብሏል፡፡ ነገር ግን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ሁለቱ አካላት ስለ ሰብዓዊ እርዳታ አቀራረብ እና የሰብአዊ መብቶችን በተመለከቱ ጉዳዮች ተነጋግረዋል ከማለት ውጭ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

የሁለቱ አካላት ውይይት የተደረገው አፍጋኒስታን የከፋ የሚባለውን የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት አርብ እለት ካስተናገደች በኋላ ነው፡፡ በሰሜናዊ ኩንዱዝ ከተማ በሚገኝ መስጊድ ላይ በተፈጸመው የአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃት ቢያንስ 50 ሰዎች ሲሞቱ ከ 100 በላይ ቆስለዋል።

ጥቃቱ የተፈፀመበት የሰይድ አባድ መስጊድ የሺዓ ሙስሊሞች ብበዛት የሚያዘወትሩት ነው የተባለ ሲሆን፣ የተለያዩ ግዛቶችን የሚያስተዳድረው ቡድን ከጥቃቱ ጀርባ እጁ እንዳለ አስታውቋል።

የአፍጋኒስታኑ ታሊባን የሾመው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሚር ካን ሙተቂ ከአሜሪካ ጋር ያደረጉት ውይይትን አስመልክቶ ሲናገሩ፣ ሁለቱ ወገኖች በ2020 የተፈረመውን የዶሃ ስምምነት ውል ለማክበር መስማማታቸውን ገልጸዋል፡፡

ይህ የዶሃ ስምምነት እንደ አልቃይዳ ያሉ ቡድኖች የአሜሪካን እና የአጋሮቿን ደህንነት አደጋ ላይ እንዳይጥሉ እርምጃዎችን ለመውሰድ ሰፊ ግዴታዎችን በታሊባን ላይ የጣለ ሲሆን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በኩላቸው የአሜሪካ ባለስልጣናት ለታሊባን የኮቪድ ክትባቶችን እና የሰብአዊ ዕርዳታን ለማድረስ ድጋፍ እንደሚያደርጉ መናገራቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የታሊባን ልኡክ ለአሜሪካ ባለስልጣናት አገሪቱ የጣለችውን የኢኮኖሚ ማእቀብ በማነሳት እንዳይንቀሳቀስ ታግዷል የተባለውን ወደ አስር ቢሊዮን ዶላር አካባቢ በድጋሚ ጥቅም ላይ እንዲውል ፍቃድ መጠየቃቸውን የአል ጀዚራ ዘገባ ያመለክታል፡፡

በነሐሴ መጀመሪያ አፍጋኒስታንን የተቆጣጠረው ታሊባን፣ በአሁኑ ወቅት ባጋጠመው የገንዘብ እጥረት ለአገሪቱ ሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞች አገልግሎት ተቋማት ገንዘብ መክፈል አለመቻሉ ይነገራል፡፡  

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img