Sunday, October 6, 2024
spot_img

ዶ/ር ምሕረት ደበበ የቀድሞ መለስ ዜናዊ አካዳሚን እንዲመሩ ተሾሙ

የሥነ አእምሮ ሐኪሙ እና በአነቃቂ ንግግሮች የሚታወቁት ዶ/ር ምሕረት ደበበ የቀድሞ መለስ ዜናዊ አካዳሚ፣ በአሁን መጠሪያው የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚን በፕሬዚዳንት እንዲመሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተሾመዋል።

ከዶ/ር ምህረት ደበበ በፊት ላለፈው አንድ ዓመት አካዳሚውን የመሩት የገዢው ብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ የነበሩት አቶ አወሉ አብዲ ሲሆኑ፣ አቶ አወሉ ባለፈው ሳምንት በተካሄደው የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ምሥረታ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ተሾመዋል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት “የመለስ ዜናዊ የአመራር አካዳሚን” ስያሜ “የአፍሪካ የአመራር ልህቀት ማዕከል” በሚል እንዲቀየር ያጸደቀው ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ነበር፡፡

አካዳሚው ከስም ለውጡ ጋር የ 21ኛው ክፍለ ዘመን የአመራር ጥያቄዎችን ለማሟላት የሚያስችል ዐቅም ያላቸውን ልሂቃን የሚያፈራ እና የዕድገት ተኮር አስተሳሰብን የሚያንፀባርቅ የትምህርት ተቋም እንዲሆን መታለሙ በወቅቱ ተገልጿል።

የአካዳሚው አዲስ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ምሕረት ደበበ በሙያቸው የአእምሮ ሕክምና ስፔሻሊስት ናቸው፡፡ የሕክምና ዲግሪያቸውን የሠሩት አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሲሆን፣ በኋላም አሜሪካ ሀገር ሄዶ በሴይንት ሊዊስ ዩኒቨርስቲ የአእምሮ ሕክምና ጥናታቸውን አጠናቀዋል፡፡

በስፋት ለአንባቢያን ባቀረቧቸው ሁለት መጽሐፍትና በአደባባይ ንግግሮቻቸው የሚታወቁት ዶክተር ምሕረት፣ ለመንግሥታዊ አገልግሎት ሲመደቡ የመጀመሪያ ጊዜያቸው መሆኑ ተነግሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዛሬው እለት ለዶክተር ምሕረት ከሰጡት ሹመት ተጨማሪ የቀድሞ የሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍሰሃ ይታገሱ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሲደረጉ፣ አቶ አብዱራህማን ሩቤ ደግሞ ምክትል እንደሆኑ አድርገዋል።

በተመሳሳይ አቶ ተስፋዬ ቤልጅጌን በሚኒስትር ማዕረግ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ፣ ዶ/ር ለገሰ ቱሉን በሚኒስትር ማዕረግ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ እንዲሁም የቀድሞን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አደም ፋራህን በሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ዋና አስተባባሪ እንዲሆኑ ሾመዋል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img