Wednesday, October 9, 2024
spot_img

በቱኒዚያ አምባገነኖችን የሚነቅፍ ግጥም የቀረበበት ቴሌቪዥን ጣቢያ ተዘጋ

 

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ መስከረም 27፣ 2014 ― በሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ቱኒዚያ አምባገነኖችን የሚነቅፍ ግጥም የቀረበበት ቴሌቪዥን ጣቢያ በአገሩ ባለሥልጣናት እንዲዘጋ መደረጉ ተነግሯል፡፡

 

ዘይቱና በተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ የቲቪ ሾው አቅራቢ የሆነው አምር አያድ፣ ባለፈው እሑድ የኢራቃዊውን ገጣሚ አሕመድ መጣርን ‹ዘ ሩለር› (‹ገዢው› እንደማለት) የተሰኘ ግጥም ማቅረቡን ተከትሎ ነው የተዘጋው፡፡

 

የአገሪቱ የፀጥታ ኃይሎች የፕሬዝዳንት ካይስ ሰዒድን አገዛዝ በመተቸት ይታወቃል የተባለውንና ኤነህዳ ፓርቲ ቅርበት አለው የሚባለውን ጣቢያ ከመዝጋታቸው በተጨማሪ የቴሌቪዥን ሾው አቅራቢውን በቁጥጥር ስር አውለዋል፡፡

 

አዣንስ ፍራንስ ፕረስ አንድ የአገሩ ባለስልጣን ጣቢያው ለዓመታት ፍቃድ ሳይኖረው በሕገ ወጥ መንገድ ሥርጭት ሲያካሄድ ነበር እንዳሉት ያስነበበ ቢሆንም፣ አገሪቱ በቅርብ ጊዜያት ፕሬዝዳንቱ ላይ ትችት የሚያቀርቡ ሕግ አውጪዎች እና ጋዜጠኞችን ማሰሯ ይነገራል፡፡

 

ለቴሌቪዥን ሾው አቅራቢው አምር አያድ እስር እንዲሁም ለዘይቱና መዘጋት ሰበብ የሆነው ኢራቃዊው ገጣሚ አሕመድ መጣር፣ በተለይ የዐረቡ ዓለም መንግሥታትን በተመለከተ በሚያቀርባቸው ግጥሞች የሚታወቅ ሲሆን፣ ስላቅ አዘል ናቸው የሚባሉት ግጥሞቹ በመሪዎቹ ላይ ጠንከር ያለ ትችት የሚሰነዝሩ ናቸው፡፡  

 

በቱኒዝያ ባለስልጣናት እንዲዘጋ የተደረገው ዘይቱና ሥርጭቱን የጀመረው በፈረንጆቹ 2012 ነበር፡፡  

 

በግጥም ሰበብ የቴሌቪዥን ጣቢያ የዘጋችው ቱኒዝያ፣ በቅርብ ወራት ከኮቪድ 19 ሳቢያ በሀገሪቱ የተከሰተውን አመጽ ተከትሎ ፕሬዝዳንቷ ካይስ ሰዒድ የሀገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ከኃላፊነት አንስተው፣ የሀገሪቱን ፓርላማ ከስራ ማገዳቸው መነገሩ አይዘነጋም።

በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ቱኒዚያውያን የሀገሪቱ መንግስት የኮቪድ 19ን የያዘበት መንገድ አግባብ አይደለም በሚል ነበር ለተቃውሞ አደባባይ የወጡት፡፡

የዓረብ ጸደይ አብዮት መነሻ የሆነችው ቱኒዚያ፣ የተሳካ የዲሞክራሲ አብዮት የተካሄደባት በሚል ስትወደስ የቆየች ቢሆንም፣ አሁን የገጠማት የፖለቲካ አለመረጋጋት ወደ ከፋ ቀውስ ሊወስዳት ይችላል የሚሉ ስጋቶች ይሰነዘራሉ፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img