Thursday, November 21, 2024
spot_img

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በትግራይ የሰብአዊ አቅርቦት ለማዳረስ በሳምንት 200 ሺሕ ሊትር ነዳጅ ያስፈልገኛል አለ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ መስከረም 24፣ 2014 ― የዓለም ምግብ ፕሮግራም በትግራይ የሰብአዊ አቅርቦት ለማዳረስ በሳምንት 200 ሺሕ ሊትር ነዳጅ ያስፈልገኛል ሲል ባወጣው ሪፖርት ላይ አስታውቋል፡፡

በክልሉ የሰብአዊ አቅርቦት ለማሳለጥ ነዳጅ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ያመለከተው የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ በአሁኑ ወቅት በክልሉ ያለው የነዳጅ አቅርቦት እየተሟጠጠ ስለመሆኑም ጠቁሟል፡፡

ከግንቦት ወር 2013 መገባደጃ አንስቶ በትግራይ ክልል ሁለተኛውን ዙር የምግብ እደላ እያከናወነ መሆኑን ያመለከተው ፕሮግራሙ፣ በሰሜን ምእራብ እና በደቡብ ትግራይ አካባቢዎች 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሰዎችን ተደራሽ ማድረጉንም ገልጧል፡፡

የትግራይ ጦርነት በተስፋፋባቸው የአፋር እና አማራ አካባቢዎች የመጀመሪያ ዙር እርዳታ አድርሶ ማጠናቁን ያስታወቀው የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ በትግራይ ክልል ለሚያደርሰው የእርዳታ አቅርቦት በሳምንት 200 ሺህ ሊትር ነዳጅ ያስፈልገኛል ብሏል፡፡

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከትግራይ በተጨማሪ ግጭት በተስፋፋባቸው የአፋር እና አማራ አካባቢዎች የመጀመሪያውን ዙር እርዳታውን ማጠናቀቁን ያስታወቀ ቢሆንም፣ አሁንም ቢሆን የመሠረታዊ አቅርቦት ችግር የታቀደውን ለማሳካት እንቅፋት እንደሆነበት ነው ያመለከተው፡፡

በጉዳዩ ላይ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር የሆኑት ሚሸል ደንፎርድ በሦስት ክልሎች የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ አዳጋች መሆኑን የጠቆሙ ሲሆን፣ በርካቶች ቤት ንብረታቸው በመውደሙ ይኸው ችግር መባባሱንም ገልጸዋል፡፡

ጦርነቱ ከነካቸው ክልሎች መካከል የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ፕሮግራም ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው መረጃ፣ በክልሉ የተስፋፋውን ግጭት ተከትሎ የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር 789 ሺሕ መድረሱን አሳውቆ ነበር፡፡ ይህንኑ ተከትሎም በክልሉ የአጠቃላይ ተፈናቃዮች ቁጥር 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን መድረሱም ነው የተነገረው፡፡

በአማራ ክልል ሕወሃት በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች በተለይ የሰብአዊ ድጋፎችን ማከናወን አስቸጋሪ ስለመሆኑ ሲነገር ቆይቷል፡፡

ባለፈው ዓመት ጥቅምት 24 የአገር መከላከያ የሰሜን እዝ የደረሰበትን ጥቃት ተከትሎ የተቀሰቀሰው ጦርነት ከጀመረ ወደ አንድ ዓመት እየተጠጋ ይገኛል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img