አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ መስከረም 19፣ 2014 ― በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተቀስቅሶ የነበረውን የኢቦላ ወረርሽኝን ለመግታት ተሰማርተው በሴቶች እና በልጃገረዶች ላይ ወሲባዊ ጥቃት ካደረሱ 83 የእርዳታ ሠራተኞች መካከል የዓለም ጤና ድርጅት ሠራተኞች እንደሚገኙበት አንድ ሪፖርት አመልክቷል።
ዘጠኝ የአስገድዶ መድፈር ክሶችን ያካተተው ይህ በደል እአአ ከ2018 እስከ 2020 ባለው ጊዜ የደረሰ ሲሆን፣ በሀገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ሠራተኞች የተፈጸመ ነው።
ሪፖርቱ ይፋ የተደረገው ከ50 በላይ የአካባቢው ሴቶች የወሲብ ጥቃት እንደተፈጸማቸውን ሪፖርት ካደረጉ በኋላ ነው። የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ጉዳዩን “ይቅርታ የማያሰጥ” ሲሉ ገልጸውታል።
ባለ 35 ገጹ ይህ ሪፖርት ምርመራ ከተደረገ በኋላ በገለልተኛ ኮሚሽን የተዘጋጀ ነው።
ሥራ ለማግኘት በልዋጩ ወሲብ እንዲፈፅሙ እንደተገደዱ የገለጹ በርካታ ሴቶችን ቃለ መጠይቅ ያደረገው ኮሚሽኑ ወንጀሉን ፈጽመዋል ተብለው ከተጠረጠሩት 83 ሰዎች መካከል 21ዱ በዓለም ጤና ድርጅት ተቀጥረው እንደሚሠሩ አረጋግጧል።
በተጨማሪም የአካባቢው ሴቶች መጠጥ ጠጥተዋል፣ በሆስፒታሎች ውስጥ “በደፈጣ” ተጠቅተዋል፣ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ለመፈጸም ተገደዋል እንዲሁም ሁለቱ አርግዘዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት እስካሁን በድርጅቱ ተቀጥረው የሚሠሩ የአራት ሰዎችን ውል ያቋረጠ መሆኑን ገልጾ ተጨማሪ እርምጃዎች እንደሚወሰዱም ቃል ገብቷል።
በትላንትናው እለት በጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት የተናገሩት ዶ/ር ቴዎድሮስ ለተጎጂዎች እና ከጥቃቱ ለተረፉት በቀጥታ ይቅርታ ጠይቀዋል።
“እናንተን ለማገልገል እና ለመጠበቅ በዓለም ጤና ድርጅት ተቀጥረው በሚሠሩ ሰዎች በደረሰባችሁ ነገር አዝናለሁ። ወንጀለኞቹ ይቅርታ እንዲደረግላቸው ሳይሆን ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ ቀዳሚ ተግባሬ ነው” ብለዋል።
በመጨረሻም ኃላፊነቱ እሳቸው ላይ እንደሆነ እና ተጎጂዎችን ለመደገፍ እና ለመጠበቅ እንደሚረዱ ቃል የገቡ ሲሆን፣ የዓለም ጤና ድርጅትን መዋቅር እና ባህል ለማስተካከልም ቃል ገብተዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጠና ዳይሬክተር ማትሺዲሶ ሞዬቲም “በሠራተኞቻቸው ድርጊት” ምክንያት የተጎዱ ሰዎችን ይቅርታ ጠይቀው፣ ግኝቶቹንም “አስፈሪ እና ልብ ሰባሪ” ብለዋል።
ኮሚሽኑ በማዕከላዊ አፍሪካዊቷ ሃገር የጾታ ብዝበዛ እና የመብት ጥሰቶችን አደጋዎች ለመቆጣጠር “ግልጽ የመዋቅር ውድቀቶች እና የዝግጁነት ማነሶችን” እንዳገኘ ገልጿል።
በዲሞክራቲክ ኮንጎ በኢቦላ ወረርሽኝ ከ2 ሺሕ በላይ ሰዎች ህይወታቸው አልፏል።
ስርጭቱን ለመግታት ዓለም አቀፍ ጥረቶችን የሚመራው የዓለም ጤና ድርጅት ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር የወረርሽኙ ማብቃት አስታውቋል።