አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ መስከረም 19፣ 2014 ― የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በጎንደር ከተማ ከህገወጥ ተኩስ ጋር በተያያዘ የከተማው ፖሊስ መሳሪያ በማስወረድ በአጥፊዎች ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን አሳውቋል።
ከትላንት ጀምሮ እስከ አሁን ሰአት ድረስ የጎንደር ከተማ ፖሊስ ከ50 የሚበልጥ የጦር መሳሪያ ማስወረዱንና ከህገወጥ ተኩስ ጋር በተያያዘ ከፖሊስ፣ ሚሊሻ፣ አድማ ብተና፣ ፌደራል ፖሊስና ልዩ ሃይል እንዲሁም የከተማው የክፍለ ከተማ እና የቀበሌ አመራሮችን ባካተተ ቡድን ትብብር ከ30 በላይ ሰዎችን አስሮ ፍ/ቤት በማቅረብ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።
የጎንደር ከተማ ፓሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር አየልኝ ታክሎ “ህብረተሰቡ የሚሰጠውን ማንኛውም ጥቆማ በመቀበል ቦታው ድረስ የፀጥታ አካላትን በመላክ ህግ የማስከበር ስራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን” ያሉ ሲሆን፣ “ህብረተሰቡ ይህን ተረድቶ ትብብሩን ሊቀጥል ይገባል” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።