Sunday, October 6, 2024
spot_img

ቻይና ክሪፕቶከረንሲን ሕገ ወጥ ስትል ፈረጀች

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ መስከረም 15፣ 2014 ― የቻይና ማዕከላዊ ባንክ ቢትኮይንን ጨምሮ ማንኛውም የክሪፕቶከረንሲ (ዲጂታል መገበያያ ገንዘብ) ግብይት ሕገ ወጥ እንዲሆን ወስኗል፡፡

‹‹ቨርቹዋል ገንዘብን በመጠቀም የሚደረግ ማንኛውም ግብይት ሕገ ወጥ የፋይናንስ እንቅስቃሴ ነው›› ያለው የቻይና ሕዝቦች ባንክ፣ ‹‹ይህ የሕዝቦችን ንብረት ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል ነው›› ሲልም አስጠንቅቋል።

የቻይና የክሪፕቶከርንሲ ገበያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ግዙፍ ከሚባሉት መካከል የሚጠቀስ መሆኑ ይነገራል፡፡

የክሪፕቶከረንሲ ገበያ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችም ሆኑ መንግሥታት በሚወስኗቸው ውሳኔዎች ምክንያት በተደጋጋሚ ከፍ እና ዝቅ እያለ ይገኛል።

ቻይና ትናንት ያሳለፈችውን ውሳኔ ተከትሎም አንድ ከረንሲ ላይ የ2000 ዶላር ቅናሽ መታየቱን የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል፡፡

ቻይና እአአ በ2019 ክሪፕቶከረንሲን መጠቀምን ብትከለክልም ግብይቱ በውጪ ምንዛሬ ሲካሄድ ቆይቷል። ነገር ግን በተያዘው ዓመት የቻይና መንግሥት ግብይቱን ለማስቆም ሰፋፊ እርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቷል።

በግንቦት ወርም የቻይና መንግሥታዊ ተቋማት በቢትኮይንም ሆነ በማንኛውም የክሪፕቶከረንሲ ለሚደረጉ ግብይቶች ሽፋን እንደማይሰጡ ገልጸው ነበር።

ይህም የመንግሥት ባለሥልጣናት በኢንዱስሪው ላይ እያደረሱት ያለው ጫና መጨመሩን ተከትሎ የመጣ ነበር።

በሰኔ ወር ላይም ባንኮችን ጨምሮ ማንኛውም የክፍያ ዘዴዎች የክሪፕቶከረንሲ ክፍያዎችን ማሳለጥ እንዲያቆሙ መንግሥት ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር። እንዲሁም ከረንሲውን የማምረት ተግባራትን ማገድም ሌላው እርምጃ ነበር።

ነገር ግን እነዚህ እርምጃዎች እንዳሉ ሆነው ትናንት አርብ የተሰጠው ውሳኔ ቻይና የክሪፕቶከረንሲን ግብይት በየትኛውም መልኩ ለማስቆም ማሰቧን ያመላከተ ነው።

እንደ መግለጫው ከሆነ ከዚህ በኋላ በግብይቱ የሚሳተፉ ሰዎች የወንጀል ተጠያቂነት ይከተላቸዋል። ይህ ብቻም ሳይሆን ይህንን አገልግሎት የሚያሳልጡ የውጪ የበይነ መረብ ገበያዎችም በሕገ ወጥ ድርጊቱ ተሳታፊ እንደሆኑ እንደሚታመንም መግለጫው አክሏል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img