አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ መስከረም 15፣ 2014 ― በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ሕወሓት በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ውስጥ የምትገኘውን ቆቦ ከተማን መቆጣጠሩን ተከትሎ የአንድ እንጀራ ዋጋ 50 ብር መግባቱን ሰሞኑን ከአካባቢው ተፈናቅለው ወደ ደሴ ከተማ የመጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ነግረውኛል ብሎ አዲስ ማለዳ ጋዜጣ አስነብቧል፡፡
ህወሓት አካባቢውን ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ የነዋሪዎቹን “እህል በሙሉ በመዝረፉ” አሁን ላይ አንድ እንጀራ 50 ብር እንደሚሸጥ እና በቦታው ያሉ ሰዎች ርሃብ ላይ መሆናቸውን የከተማው ነዋሪዎች መግለጻቸው ተመላክቷል፡፡
“አስር ብር የነበረው እንጀራ 50 ብር ነው ስንገዛ የነበረው” ያሉት ኗሪዎቹ፣ ዋጋው የጨመረበት ምክንያትም እንጀራውን መግዛት የሚቻለው ከትግራይ ክልል መጥተው በቆቦ ከተማ ከሰፈሩት ነጋዴዎች ብቻ ስለሆነ ነው ብለዋል።
ጋዜጣው የአካባቢው ነዋሪዎች ከመዘረፍ ያተረፉትን ብር በመጨረሳቸው እና በእያንዳንዱ ሸቀጥ ላይ ከልክ ያለፈ የዋጋ ጭማሪ በመከሰቱ የዕለት ምግባቸውን መግዛት አለመቻላቸውን ከነዋሪዎች ተረድቻለሁ ብሏል፡፡
የትግራይ ተወላጆች በቆቦ ከተማ በጀመሩት የንግድ እንቅስቃሴ በእያንዳንዱ ዕቃ ላይ የዋጋ ጭማሪ ተደርጎ አስር ብር ሲገዛ የነበረው ሻማ 60 ብር፣ 120 ብር የነበረው አንድ ሊትር ዘይት 390 ብር፣ አራት ብር የነበረው ክብሪት 13 ብር፣ ሁለት ብር የነበረው ዳቦ 10ብር መሆኑንም በዘገባው ተመላክቷል፡፡
በሌላ በኩል የአንድ ኪሎ ዱቄት ዋጋ 70 ብር እንደሚሸጥ የተገለጹ ሲሆን፣ “መነገድ የሚችለው የትግራይ ተወላጅ ብቻ ነው” በማለት አንድ ኩንታል ዱቄት 2ሺሕ ብር ሲሸጡ የነበሩት የአካባቢውን ተወላጆች “ለምን በቅናሽ ዋጋ ትሸጣላችሁ’’ ተብለው ከንግድ ሥራቸው እንደተባረሩ እና የትግራይ ተወላጆቹም አንድ ኩንታል ፉርኖ ዱቄት 7ሺሕ ብር እየሸጡ መሆናቸውን በዘገባው ስማቸው የተጠቀሰ ነዋሪ ተነግረዋል፡፡
በተጨማሪም ህወሓት በተቆጣጠረው አካባቢ የቀሩ ሰዎች “ከሁለት ወር ጀምሮ በርሃብ ከመቀጣታቸውም በተጨማሪ፣ በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት ጳጉሜን አራት 2013 በሰነዘረው ጥቃት ከ600 በላይ ንጹኃን በግፍ ተገድለዋል’’ ሲል ነዋሪዎቹ መናገራቸው ሰፍሯል፡፡
አቅመ ደካማ አዛውንቶች ጭምር ደርሶባቸዋል በተባለው ጥቃት፣ ሰኞ ገበያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በተሰነዘረው የፈንጂ ጥቃት ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ የቀን ሠራተኞችና የከተማው ገበሬዎች መገደላቸውን በአካባቢው የነበሩ የዐይን እማኞች አብራርተዋል። “ሁለት ወር ሙሉ ለፈለፍን፣ ግን ሰሚ የለም” የሚሉት ነሪዎቹ፣ ከሞት ተርፈው በርሃብ ላይ ላሉት ሰዎች ቢያንስ ቀይ መስቀል እንኳን ሊደርስላቸው ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።