አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ መስከረም 12፣ 2014 ― የታሊባን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አሚር ካህን ሙታቂ በላኩት ደብዳቤ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ታሊባን ንግግር እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
አፍጋኒስታንን ማስተዳደር ከጀመረ ሳምንታትን ያስቆጠረው ታሊባን፣ በኒው ዮርክ እየተካሄደ ባለው የተባበሩት መንግሥታት አባል አገራት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ንግግር ለማድረግ ጥያቄውን አቀረበ።
የታሊባን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አሚር ካህን ሙታቂ ሳለፍነው ሰኞ በላኩት ደብዳቤ ነው ጥያቄውን ያቀረቡት።
ጉዳዩ የሚመለከተው የመንግሥታቱ ድርጅት ኮሚቴ ጥያቄውን እያጤነው መሆኑ የተነገሩ ሲሆን፣ ምላሽ እስከሚሰጥ እየተጠበቀ ነው። አሜሪካ፣ ቻይና እና ሩሲያ የኮሚቴው አባል መሆናቸውንም የተመድ ቃል አቀባይ ተናግረዋል።
ነገር ግን ጠቅላላለ ጉባኤው በመጪው ሰኞ ከመጠናቀቁ በፊት ኮሚቴው ይሰበሰባል ተብሎ አይጠበቅም። እስከዛ ድረስም የቀድሞው የአፍጋኒስታን አምባሳደር መቀመጫቸውን ይዘው ይቀጥላሉ መባሉንም የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል።
ታሊባን በተጨማሪም በኳታር ዶሃ መቀመጫው ያደረገውን የቡድኑን ቃል አቀባይ ሲሃሊ ሻሂንን በተመድ የአፍጋኒስታን አምባሳደር አድርጎ አጭቷል። እንዲሁም የቀድሞው የአገሪቱ ልኡክ ከዚህ በኋላ አፍጋኒስታንን አይወክልም ሲል ታሊባን ለተመድ ገልጿል።
ምንም እንኳን ታሊባን ከዚህ በኋላ አፍጋኒስታንን አይወክሉም ቢልም አምባሳደሩ በጉባኤው የመጨረሻ ቀን በተመድ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎም ይጠበቃል።
ታሊባን አክሎም በርካታ አገራት አፍጋኒስታንን ለቀው ወደ አረብ ኤምሬቶች የተሰደዱትን የቀድሞውን ፕሬዝዳንት አሽራፍ ጋኒን ከዚህ በኋላ እንደ መሪ አይመለከቷቸውም ብሏል።
እኤአ ከ1996 እስከ 2001 ታሊባን አፍጋኒስታንን በተቆጣጠረባቸው ዓመታት የቀደመው መንግሥት አምባሳደር ጉዳይን የሚመለከተው ይሄው ኮሚቴ ስምምነት ላይ መድረስ ባለመቻሉ ሳይነሱ ቆይተው ነበር።
ኳታር ማክሰኞ ዕለት በነበረው ጉባኤ ላይ ባደረገችው ንግግር የአገራቱ መሪዎች ከታሊባን ጋር እንዲሰሩ ጥያቄ አቅርባለች።
“ታሊባን ላይ አድማ ማድረግ ቡድኑን ወደ ጽንፈኝነት ይመራዋል። ነገር ግን ውይይት የተሻለ ፍሬ ያመጣል” ሲሉ የኳታሩ መሪ ሼክ ታሚም ቢን ሃማድ አል ታኒ ተናግረዋል።