Tuesday, October 8, 2024
spot_img

የመንግሥታቱ ድርጅት ኤርትራ ለሃያ ዓመታት ያሰረችውን ጋዜጠኛ ዳዊት ይስሐቅን እንድትፈታ ጠየቀ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ነሐሴ 13፣ 2013 ― የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሙያዎች ለሃያ ዓመታት ያህል ያለ ፍርድ የታሰረው ኤርትራዊ ጋዜጠኛ ዳዊት ይስሃቅ በአስቸኳይ እንዲፈታ ጠይቀዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት አጣሪ እንዳሉት ከሆነ ጋዜጠኛ ዳዊት ይስሃቅ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ክስ ያልተመሠረተበት ሲሆን፣ ጠበቃውንም አግኝቶ አያውቅም።

የሰብዓዊ መብት አጣሪዋ ዳዊት ይስሃቅ በህይወት አለ የሚለው ጉዳይ ላይ ፍራቻ እንዳለ ገልፀው፣ የኤርትራ ባለሥልጣናት የጋዜጠኛውን በህይወት መኖር ማስረጃ እንዲያቀርቡም አሳስበዋል።

ጋዜጠኛና ገጣሚው ዳዊት ይስሃቅ ነፃ ኤርትራን አገለግላለሁ በማለት ወደ ትውልድ አገሩ ተመልሶም የለውጥ ደጋፊ የሆነ ጋዜጣም አቋቁሞ ነበር።

የስዊድንና ኤርትራዊ ዜግነት ያለው ዳዊት በአውሮፓውያኑ ዘመን ቀመር 1990ዎቹ በአገሪቱ ውስጥ ከመጀመሪያዎቹ ነፃ ጋዜጦች ውስጥ አንዱን ያቋቋመ ስለመሆኑ ይነገርለታል፡፡

ጋዜጠኛ ዳዊት በጋዜጣው የፖለቲካ ተሃድሶን ከሚሹ ፖለቲከኞች የተላከ ግልፅ ደብዳቤ ካሳተመ በኋላም ነው ለእስር የተዳረገው።

ጋዜጠኛው ቤተሰቡን፣ ጠበቃውን እንዲሁም በተደጋጋሚ ከተባበሩት መንግሥታትም ሆነ የስዊድን ተወካዮች እንዲያገኙት ጥያቄ ቢቀርብም ማንም ጎብኝቶት አያውቅም።

በህይወት እንዳለ የተጠረጠረው በጎሮጎሳውያኑ 2005 ሲሆን፣ በእስር ላይ በፈታኝ ሁኔታ እንደሚገኝም ተጠቁሟል።

ከጋዜጠኛው እስር ጋር በተያያዘም ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን (አርኤስኤፍ) የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን በሰብዓዊነት ላይ በሚፈፀሙ ወንጀሎች ክሱን ስዊድን ለሚገኘው ዐቃቤ ሕህግ ከወራት በፊት አቅርቧል።

ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ በተጨማሪ ሰባት ከፍተኛ ባለሥልጣናትንም በሰብዓዊነት ላይ በሚፈፀሙ ዓለም አቀፍ ወንጀሎች ቡድኑ ወንጅሏቸዋል።

ባለሥልጣናቱ ጠንከር ያለ ምርመራ እንዲከፈትባቸው፣ ጋዜጠኛውን በማገት፣ በማንገላታትና ያለበትንም ደብዛ በማጥፋት ክስ ይመሰርትባቸዋል ብሎም እንደሚያንም ቡድኑ በወቅቱ በድረ-ገፁ አስፍሯል።

በዓለም ላይ ለረዥም ዓመታት በእስር ላይ የሚገኝ ጋዜጠኛ እንደሆነም ተገልጿል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img