አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ነሐሴ 5፣ 2013 ― የአሜሪካው የደኅንነት ተቋም ሲአይኤ አለቃ ዊሊያም በርንስ በኢራን የኒኩለር ጉዳይ ለመምከር የመጀመሪያ የእስራኤል ጉብኝቸውን ማድረጋቸው ተሰምቷል፡፡
ሚድል ኢስት ሞኒተር ይዞት እንደወጣው ዘገባ ከሆነ ዊሊያም በርንስ በእስራኤል ቆይታቸው የሞሳድ ዳይሬክተር የሆኑት ዴቪድ ባርኒያ እና የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት እንዲሁም የደህንነት እና የመከላከያ ሹሞችን ያገኛሉ ተብሏል፡፡
የአሜሪካው የደኅንነት ተቋም አለቃ ወደ እስራኤል ያቀኑት በሂዝቦላህ እና እስራኤል መካከል ያለው ሁኔታ በተካረረበት ወቅት መሆኑንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
ዊሊያም በርንስ ከእስራኤል ሹማምንት ተጨማሪ ወደ ፍልስጤም አቅንተው የፍልስጤሙን ፕሬዝዳንት ማሕሙድ አባስ፣ የደህንነት አለቃው መጂድ ፈረጅ እና ሌሎችንም አግኝተው ከእስራኤል የደህንነት ጉዳዮች ትብብር በማድረግ ዙሪያ ይመክራሉ መባሉም ተመላክቷል፡፡