አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ነሐሴ 4፣ 2013 ― የፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በእነ አቶ እስክንደር ነጋ ላይ የሚያቀርባቸውን ምስክሮች በግልጽ ችሎት እንዲያሰማ የሥር ፍርድ ቤቶች የሰጡትን ውሳኔ በመቃወም ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ላቀረበው አቤቱታ ምላሽ የሰጡት እነ እስክንድር ነጋ (አራት ተከሳሾች)፣ ሰበር ሰሚ ችሎቱ በአገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የዳኝነት ሥልጣን ያለው ተቋም በመሆኑ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ሲሰጥ፣ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚው ችሎት ያሳዩትን የዳኝነት ነፃነት፣ ሰበር ችሎቱም በመድገም የዓቃቤ ሕግን አቤቱታ ውድቅ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡
ተከሳሾቹ ሐምሌ 28፣ 2013 ለሰበር ችሎቱ ባቀረቡት ምላሽ እንደገለጹት፣ ከመነሻው የእነሱን ጉዳይ በወንጀል ችሎት እንዲታይ የተደረገበት ዋና ምክንያት ወንጀል ተፈጽሞ ሳይሆን፣ ዓቃቤ ሕግ በአንድ በኩል የፖለቲካ ተቋም እንደ መሆኑ መጠን፣ ፖለቲካዊ ዓላማና ግብ ይዞ በመነሳት እነሱ በአዲስ አበባ ተፅዕኖ የሚፈጥር የፖለቲካ ፓርቲ በመመሥረታቸውና ከስድስተኛው ብሔራዊ ምርጫ ገለል እንዲደረጉና ለመበቀል ታስቦ የቀረበ ክስ ነው፡፡
ገዥው ፓርቲ እነሱን ለመበቀል ጥረት እያደረገ ያለው በውጤቱ ብቻ ሳይሆን በሒደቱም፣ በየትኛውም አገር ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ የምስክር አሰማም ሒደቱን በዝግና ከመጋረጃ ጀርባ በማድረግ፣ በተለያዩ ደረጃዎች ያስጠኗቸውን የሊግ አባላት በማቅረብ፣ ተጠሪዎችን ከመበቀል ጎን ለጎን ችሎቱንም የሊግ አባላት መጫወቻ ለማድረግ አስቦ ያቀረበው አቤቱታ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመ.ቁ 199376 ግራቀኛችንን አከራክሮ ግንቦት፣ 2013 በሰጠው ፍርድ፣ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የምስክሮችን አሰማምን በተመለከተ መስከረም 4፣ 2013 የሰጠውን ውሳኔ እንደገና እንዲያይና ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው አቤቱታ በምስክሮ ላይ የተረጋገጡ አደጋዎችና ሥጋቶችን በሚመለከት በበቂ ምክንያትና ማስረጃ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቶ፣ መዝገቡን ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመመለስ ግራ ቀኙን ማከራከሩን ተከሳሾቹ በመልሳቸው አስረድተዋል። ዓቃቤ ሕግ ምስክሮቹ በዝግና ከመጋረጃ ጀርባ እንዲሰሙ የሚያስችሉ በበቂና አሳማኝ ምክንያቶችና ማስረጃዎች ማረጋገጥ ባለመቻሉ፣ ፍርድ ቤቱ ማመልከቻውን ውድቅ እንዳደረገውም አክለዋል።
ዓቃቤ ሕግ ግን የሥር ፍርድ ቤትን ውሳኔ በመቃወም ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ ያቀረበ ቢሆንም፣ ችሎቱ በመዝገብ ቁጥር 210614 በሰጠው ውሳኔ ‹‹አያስቀርብም›› በማለት ሐምሌ 7፣ 2013 መዝገቡን እንደዘጋውም አስታውሰዋል፡፡ በመሆኑም በምስክሮቹ ላይ የተጋረጡ አደጋዎችና ሥጋቶችን በበቂ ምክንያትና ማስረጃ ማቅረብ አለማቅረብ በፍሬ ነገር የሚታይ ካልሆነ በስተቀር፣ በምንም ሁኔታ መሠረታዊ የሕግ ስህተቶችን ለሚመረምር ችሎት ሊቀርብ የማይገባው ክርክር መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ጉዳዩ ሰበር ችሎቱ ከተቋቋመበት ተፈጥሯዊ የዳኝነት ሥልጣን ጋር የሚቃረን በመሆኑና የፍሬ ነገር እንጂ መሠረታዊ የሕግ ጉዳይ ባለመሆኑ፣ ችሎቱ የሥር ፍርድ ቤቶች ውሳኔን በማፅናት መዝገቡ እንዲዘጋላቸው ጠይቀዋል፡፡
ተከሳሾቹ በምላሻቸው እንዳብራሩት፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 199376 ግራ ቀኙን አከራክሮ ግንቦት 4 2013 ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት መዝገቡን ሲመልሰው ዓቃቤ ሕግ ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታ ባላቀረበበት ሁኔታና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ፣ ችሎት የሰጠውን ውሳኔ ተቀብሎ፣ ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመመለስ በጉዳዩ ላይ በድጋሚ ተመልሰው ክርክር ማድረጋቸውንና ክርክሩ ውሳኔ ካገኘ በኋላ፣ ቀደም ሲል ቀርበው የሰበር አቤቱታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ መነሻ አድርጎ ይግባኝ ከጠየቀ በኋላ፣ ‹‹ጉዳዩን ወደ ሥር ፍርድ ቤት ሊመልሰው አይገባም›› በሚል የሚያቀርበው መከራከሪያ ሥነ ሥርዓታዊ ካለመሆኑም በላይ ከሥር ፍርድ ቤት እስከ ሰበር ድረስ ወጥነት የሌለውና የተበጣጠሰ ቅሬታ ያቀረበ መሆኑን የሚያሳይ መሆኑን አብራርቷል፡፡ ስለሆነም የቀረበው መከራከሪያ መሠረታዊ የሥነ ሥርዓት ስህተት ያለበት መሆኑን አስረድተው ውድቅ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡
ዓቃቤ ሕግ ምስክሮቹ በዝግና ከመጋረጃ ጀርባ እንዲሰሙለት ሲያመለክት በምስክሮች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 አንቀጽ 5(1)ን ብቻ መሠረት በማድረግ መሆኑንና ይህም የጥበቃ ተጠቃሚው ሊደርስበት ይችላል ተብሎ የሚገመተውን የአደጋ ሁኔታ ብቻ መሠረት በማድረግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በአዋጁ አንቀጽ 5 (3) ላይ በግልጽ እንደተጠቀሰው ለምስክሮች ጥበቃ ሊሰጥ የሚችለው የጥበቃ ተጠቃሚው ሊደርስበት ይችላል ተብሎ የሚገመተውን የአደጋ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን፣ በሌላ ሰው መብትና ሕጋዊ ጥቅም ላይ የሚያስከትለውንም ጉዳት ከግምት በማስገባት ሊሆን እንደሚገባ መደንገጉን አስታውሰዋል፡፡ የእነሱንም መሠረታዊ መብትና ነፃነት የማክበርና የማስከበር ኃላፊነትና ግዴታውን በመተው፣ ዓቃቤ ሕግ አዋጁን በሚፈልገው መንገድ ብቻ እየተረጎመ ፍርድ ቤት እንዲያፀድቅለት ብቻ የሚያቀርበው መከራከሪያ የፍርድ ቤትን ተፈጥሯዊ ባህሪ ወደ ጎን የተወና ፍርድ ቤቶችንም የፖለቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያ እንደሆኑ ለማድረግ ታስቦ የቀረበ መከራከሪያ መሆኑን በመጠቆም፣ ችሎቱ የዓቃቤ ሕግን መከራከሪያ ውድቅ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡
ዓቃቤ ሕግ በምስክሮች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/03 አንቀጽ 4 (1 ቀ እና በ) መሠረት ያሉትን የጥበቃ ዓይነቶች የመረጠበት ዋና ዓላማ በተጨባጭ በምስክሮች ላይ የሚደርስ አደጋ ኖሮ ሳይሆን፣ ክሱ ፖለቲካዊ ዓላማና ግብ ያለው በመሆኑና ከእያንዳንዱ የፍርድ ሒደት እነሱን ለመበቀልና ሌሎች መንግሥትን በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉትን ለማስጠንቀቅ አስቦ የመረጠው የጥበቃ ዓይነት መሆኑን ጠቁሟል መባሉን የዘገበው ሪፖርተር ነው፡፡