Sunday, September 22, 2024
spot_img

በእነ እስክንድር ነጋ ላይ የሚቀርቡ ምስክሮችን የመስማት ሂደት በድጋሚ ለሌላ ቀን ተዛወረ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ሐምሌ 9፣ 2013 ― የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በእነ እስክንድር ነጋ ላይ የቆጠራቸውን ምስክሮች ዛሬም በችሎት ፊት ማቅረብ ባለመቻሉ የምስክር መስማቱ ሂደቱ በድጋሚ ለሌላ ቀን ተዛውሯል። ዐቃቤ ህግ ምስክሮቹን በመጪው ሳምንት እንደሚያቀርብ ዛሬ ለችሎቱ ገልጿል።

የእነ እስክንድርን ጉዳይ የሚመለከተው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የፀረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ችሎት፤ ዐቃቤ ህግ ከዛሬ ጀምሮ ምስክሮቹን ማሰማት እንዲጀምር ትዕዛዝ የሰጠው ትላንት ሐሙስ ሐምሌ 8 በነበረው ውሎው ነው። ዐቃቤ ህግ ምስክሮቹን ማቅረብ ያልቻለው “የምስክሮችን ደህንነት እና ጥበቃ ለማረጋገጥ ጊዜ ስለሚያስፈልግ” በሚል ምክንያት ነበር።

ፍርድ ቤቱ ያቀረበውን ጥያቄ ውድቅ እንዳደረገበት በዛሬው ችሎት የጠቀሰው ዐቃቤ ህግ፤ “መብታችን ስለሆነ ቀድሞ በተያዘው አጀንዳ መሠረት [ምስክሮቻችንን] በ15 እና 16 እናሰማለን’’ ብሏል። እስከዚያ ድረስም ለምስክሮች ጥበቃ የሚያስፈልጉ ተግባራትን እንደሚያከናውን አስረድቷል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሰኔ 22፤ 2013 በዋለው ችሎት፤ ዐቃቤ ህግ በተከሳሾች ላይ የቆጠራቸው ምስክሮች በሐምሌ 8፣ 9፣ 14፣ 15 እና 16 በግልጽ ችሎት እንዲሰሙ ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል። ከተከሳሾች ጠበቃ አንዱ የሆኑት አቶ ሔኖክ አክሊሉ፤ ምስክር አሰማሙ በአምስት ቀናት የተከፋፈለው ምስክሮች ብዙ ስለሆኑ እና በሁለትና በሶስት ቀናት ስለማያልቅ ነው ብለዋል።

ዐቃቤ ህግ “ምስክር በሚያቀርብበት ቀን ‘ቆይ ለምስክሮች የማደርገውን ጥበቃ አልጨረስኩም’ የሚለው ክርክር ውሃ የሚቋጥር አይደለም” ሲሉ የተከራከሩት ጠበቃ ሔኖክ፤ ከሁኔታው ዐቃቤ ህግ “ምስክር ማሰማት እንዳልፈለገ ነው የምንረዳው’’ ሲሉ በትላንትናው ችሎት ያነሱትን “ክሱ ይቋረጥ” ጥያቄ ደግመው አቅርበዋል።

ሌላኛው የተከሳሾች ጠበቃ ቤተማሪያም አለማየሁ በበኩላቸው የዐቃቤ ህግ ቀጠሮ አለማክበር “በተከሳሾች መሠረታዊ መብት ላይ ጉዳት አለው” ሲሉ ለችሎቱ ተናግረዋል። ዐቃቤ ህግ ምስክር ማሰማት በፈለገ ጊዜ መዝገቡን የማንቀሳቀስ መብቱ ተጠብቆ ክሱ እንዲቋረጥም ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ ዐቃቤ ህግ በትላንትናው ችሎት የጠየቀውን ተለዋጭ የጊዜ ቀጠሮ ውድቅ ማድረጉን አስታውሷል። ዐቃቤ ህግ ምስክሮቹን እሱ በፈለገው ጊዜ ሳይሆን ከዚህ ቀደም በተሰጠው ጊዜ መሰረት ከሐምሌ 14 እስከ 16 ባሉት ሶስት ቀናት እንዲያሰማ አዝዟል።

ፍርድ ቤቱ ከዚህ በተጨማሪም በትላንትናው የችሎት ውሎ፤ ሁለተኛ ተከሳሽ አቶ ስንታየሁ ቸኮል የ“ዘለፋ” አገላለጽ ተጠቅመዋል በሚል በዐቃቤ ህግ የቀረበውን “ቅጣት ይጣልባቸው” የሚለውን ጥያቄ ተመልክቷል። አቶ ስንታየሁ “ችሎት ላይ በሚከራከሩበት ሰዓት የሚናገሩትን ነገር እንዲቆጥቡ እና ችሎቱን እንዲያከብሩ” ሲል ፍርድ ቤቱ በተግሳጽ አልፏቸዋል። ሁለተኛው ተከሳሽ ዘለፋ ፈጽመዋል ያስባለው ንግግራቸው፤ “ዐቃቤ ህግ በውሸት ስላሳሰረን እናመሰግናዋለን” የሚለው አገላለጻቸው እንደነበር የዘገበው ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ነው።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img