Monday, September 23, 2024
spot_img

ድምጻዊ ሐጫሉ ሁንዴሳን በመግደል ጥፋተኛ የተባለው ተከሳሽ በሞት እንዲቀጣ ዐቃቤ ህግ ጠየቀ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ሐምሌ 8፣ 2013 ― ድምጻዊ ሐጫሉ ሁንዴሳን በመግደል ጥፋተኛ የተባለው አንደኛ ተከሳሽ ጥላሁን ያሚ በሞት እንዲቀጣ ዐቃቤ ሕግ ጠየቀ። ዐቃቤ ህግ የሞት ፍርዱን የጠየቀው ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ የፀረ ሽብር እና ሕገ መንግሥታዊ ችሎት ባቀረበው የቅጣት አስተያየት መሆኑን ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘግቧል፡፡

ዐቃቤ ሕግ በዛሬው እለት ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው የቅጣት ማክበጃ፤ ተከሳሹ ከዚህ በፊት በባጃጅ እና የባቡር ሐዲድ ሥርቆት ተከስሶ እንደነበረ እና በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ክሱ መቋረጡን አንስቷል።

ተከሳሹ ‛‛ነውጠኛ ባህሪ እንዳለው ከምስክር መሰማቱን’’ በተጨማሪ የቅጣት ማክበጃነት የጠቀሰ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ የተከሳሹን የቅጣት ማቅለያ ሳይመለከት የሞት ፍርድ ብያኔ እንዲሰጥ ዐቃቤ ሕግ ጠይቋል።

ሁለተኛ ተከሳሽ ከበደ ገመቹን በተመለከተ ለቤት መስሪያ በተሰጠው ገንዘብ “ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ መግዛቱን” የተከሳሽ እናት መመስከራቸውን ያስታወሰው ዐቃቤ ህግ፤ ፍርድ ቤቱ በተከሳሹ ላይ በቅጣት አወሳሰን መመሪያ መሰረት እንዲወስንለት ጠይቋል።

ሦስተኛ ተከሳሽን በተመለከተ አብዲ አለማየሁን በተመለከተ ፍርድ ቤቱ በራሱ የቅጣት ውሳኔ እንዲሰጥ ዐቃቤ ህግ ጥያቄ አቅርቧል። ፍርድ ቤቱ የሶስተኛ ተከሳሽን የቅጣት ማቅለያ ቢቀበለው ተቃውሞ እንደሌለውም ገልጿል።

ለሦስቱም ተከሳሾች በመንግስት በኩል የተመደቡት ተከላካይ ጠበቃ “ተከሳሾች የቀድሞ ባህሪያቸው ታይቶ ማቅለያ ይያዝላቸው” ሲሉ የቅጣት ማቅለያ አስተያየት አቅርበዋል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ የፀረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ችሎት የቅጣት አስተያየቱን መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ለሐምሌ 20፤ 2013 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። ተከሳሾች ተጨማሪ የቅጣት ማቅለያ ካላቸው ከቀጠሮው ቀን በፊት በፍርድ ቤት ሬጅስትራር በኩል እንዲያቀርቡም ፍርድ ቤቱ አዝዟል።

(ፎቶ፡ አመንሲሳ ኢፋ እና ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት)

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img