Saturday, November 23, 2024
spot_img

የሲዳማ ክልል ልዩ ኃይል ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ሽኝት እንደተደረገለት ተሰማ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ሐምሌ 8፣ 2013 ― የሲዳማ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ትላንት ማምሻውን በሐዋሳ ከተማ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ የሽኝት መርሐ ግብር እንደተደረገላቸው ተሰምቷል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የክልሉ ሰላምና ፈጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ ጢሞቲዎስ፣ የክልሉ ካቢኔዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል ነው የተባለው፡፡

አቶ ዓለማየሁ የክልሉ ልዩ ኃይል ወቅቱ ለሚፈልገው ሀገራዊ ተልዕኮ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም ግዳጁን እንደሚወጣ ነግረውኛል ብሎ ኢዜአ ዘግቧል፡፡

አክለውም ‹‹የልዩ ኃይሉ አባላትም ሀገራዊ ጥሪውን በታላቅ ወኔና ደስታ ተቀብለው ለመዝመት ያላቸው መነሳሳት ከፍተኛ ነው›› ማለታቸውም ተመላክቷል፡፡

በሐዋሳ ከተማ በሚገኝ ሆቴል በተካሄደው የሽኝት መርሃ ግብር ላይ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ደስታ ሌዳሞ ተገኝተዋል።

ከሲዳማ ልዩ ኃይል የሰሜን ኢትዮጵያ ዘመቻ ጋር በተገናኘ፣ የልዩ ኃይሉ አባላት ‹‹በሰሜኑ ጦርነት አንሳተፍም በማለት ሐዋሳን ለቀው ወደ ቤተሰብ እና ዘመድ›› ጋር ተበትነዋል በሚል ማለዳ የተሰኘ የበይነ መረብ ሚዲያ ዘግቦ ነበር፡፡

በጉዳዩ ላይ ኢትዮጵያ ቼክ የተባለ መረጃ አጣራለሁ የሚል ድረ ገጽ፣ የሲዳማ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞን በስልክ አግኝቼ የበይነ መረብ ሚዲያው ያሠራጨው መረጃ ‹‹ሐሰተኛ ነው›› ብለውኛል ሲል አስነብቦ ነበር፡፡ ርእሰ መስተዳደሩ ዘገባውን ‹‹የሲዳማ ሕዝብ ድጋፉን እንዳይሰጥ ለማድረግ የሚደረግ ጥረት ነው፤ የሚሸኙ አሉ፣ በፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው ሚድያዎች ስለሚዘግቡ በግልፅ ታዩታላችሁ›› ማለታቸውም ተመላክቶ ነበር፡፡

ሆኖም ለርእሰ መስተዳደሩ አስተያየት የመልስ መልስ የሰጠው ማለዳ ሚዲያ፣ የርእሰ መስተዳደሩን ውንጀላ በማጣጣል፣ በትላናትናው እለት የልዩ ኃይሉ መበተን ‹‹የፀጥታ ክፍተት ስለፈጠረ ሐዋሳ ከተማ የሚገኙ ወሳኝ ሥፍራዎች በፌደራል ፖሊስ እና መከላከያ ሲጠበቅ መዋሉን›› ሰምቻለሁ ብሎ የዘገበ ሲሆን፣ ‹‹የፌደራል ፖሊስ በከተማው ቅኝት ሲያደርግ›› መስተዋሉንም አክሏል፡፡

የመንግሥት ሚዲያዎች በበኩላቸው ትላንት ምሽት ልዩ ኃይሉን አስመልክቶ ይዘው በወጡት መረጃ፣ በምስል አስደግፈው ሽኝቱን አሳይተዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img