አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ሐምሌ 7፣ 2013 ― በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ግጭት ተከትሎ ወደ ሥፍራው እንዲቀኑ ትእዛዝ የወረደላቸው የሲዳማ ልዩ ኃይል አባላት በጦርነቱ አንሳተፍም በማለት የነበሩበትን ሐዋሳ ካምፕ ለቅቀው መውጣታቸውን ማለዳ ሚዲያ ዘግቧል፡፡
ትእዛዙን ተቃውመዋል የተባሉት የልዩ ኃይል ፖሊስ አባላት ወደ ቤተሰብ እና ዘመዶቻቸው በመበተናቸው ካምፕ ውስጥ የቀሩት ከ10 የማይበልጡ አመራሮች ብቻ መሆናቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
የክልሉ ካድሬዎች በመጀመሪያ ዙር 200 ልዩ ኃይሎችን መልምለው ለመላክ እየተሰናዱ እንደነበር የተነገረ ሲሆን፣ ልዩ ኃይሉን በጦርነቱ የማሳተፍ ጉዳይ በክልሉ አመራሮች መካከልም ልዩነት መፍጠሩን ማለዳ ሚዲያ በዘገባው ጠቋሟል፡፡
ከዚሁ ጋር በተገናኘ ልዩ ኃይሎቹ ትእዛዝ አልተቀበሉም በተባለበት ሲዳማ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልሎች እያንዳንዱ ቀበሌ 10 ሚሊሻዎችን እንዲያቀርብ ታዟል መባሉንም ዘገባው ያመለክታል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ የአማራ እና የትግራይ ክልልን በሚያዋስኑ እና ከስምንት ወራት በፊት በተቀሰቀሰው ጦርነት በአማራ ልዩ ኃይል ቁጥጥር ስር በወሉ አካባቢዎች ላይ በአሁኑ ወቅት ጦርነት እንደተከፈተ የተነገረ ሲሆን፣ ግዛት አስመልሳለሁ በሚል ጦርነቱን ማወጁ የተነገረው ሕወሃት ኮረም እና አላማጣን ተቆጣጥሬያለሁ ማለቱም ይታወሳል፡፡
የትግራይ ክልልን የሚዋሰነው የአማራ ክልል መንግሥት በበኩል ትላንት ምሽት ባወጣው መግለጫ ሕወሃት ከትግራይ በሚያዋስኑ ሁሉም አቅጣጫዎች መጠነ ሰፊ ወረራና ጥቃት እየፈጸመብኝ ይገኛል ብሏል።
የክልሉ መንግሥት እንመክተዋለን ያለውንና ከሕወሃት ጋር አደርገዋለሁ ያለውን ጦርነት፣ ‹‹ለሕዝባችን ህልውናና ለሀገር ሉአላዊነት መሆኑ ግንዛቤ ውስጥ ገብቶ የጋራ ጠላታችንን በጋራ እንድንፋለመው›› በማለት ጥሪ አቅርቧል፡፡