Sunday, September 22, 2024
spot_img

ወደ መቀሌ እና ሰመራ ይጓዙ የነበሩ የዓለም የምግብ ፕሮግራም የጭነት ተሽከርካሪዎች ከሰሜን ወሎ እንዲመለሱ መደረጋቸው ተሰማ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ሐምሌ 1፣ 2013 ― የእርዳታ እህል ጭነው ወደ መቀሌ እና ሰመራ ከተሞች ሲጓዙ ነበሩ የተባሉ የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) ዘጠኝ የጭነት ተሽከርካሪዎች፤ ከአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ወደመጡበት እንዲመለሱ መደረጋቸውን የአካባቢው ባለስልጣናት ተናግረዋል፡፡

በሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ፤ ፍላቂት ገርገራ ከተማ ለሶስት ቀናት እንዲቆሙ ተደርገው የነበሩት ተሽከርካሪዎች፣ በዛሬው ዕለት እንዲመለሱ የተደረገው በአካባቢው ያለው ህዝብ “አላሳልፍም” በማለቱ በመሆኑ ባለስልጣናቱ ገልጸዋል።

የመቄት ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ በሪሁን ተረፈ፤ የዓለም ምግብ ፕሮግራም መለያ የለጠፉ ተሽከርካሪዎች ወደ ወረዳቸው የደረሱት ከትናንት በስቲያ መሆኑን ተናግረዋል።

ተሽከርካሪዎቹ የወረዳው ዋና ከተማ በሆነችው ፍላቂት ገርገራ እንዲቆሙ የተደረገው፤ የአካባቢው ነዋሪዎች ተሽከርካሪዎቹን “ማገት ስለፈለገ ነው” ብለዋል።

በዓለም ምግብ ፕሮግራም ተሽከርካሪዎች የተጫነውን እርዳታ “እናውርድ” እና ለተፈናቃዮች “እናከፋፍል” ይሉ የነበሩት ወጣቶች፣ “ኢ-መደበኛ አደረጃጀት” ያላቸው እንደሆነ የጠቀሱት የወረዳው አስተዳዳሪ፤ በዚህም ምክንያት የተሽከርካሪዎቹን ደህንነት ለማስጠበቅ “ፖሊስ ጣቢያ አካባቢ” እንዲቆዩ መደረጋቸውን አስረድተዋል።

የመቄት ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ወዳጄ መኮንን “መኪኖቹ ለራሳቸው ደህንነት ሲባል ነው እንዲቆሙ የተደረገው” ሲሉ የአስተዳዳሪውን ሃሳብ የሚያጠናክር አስተያየት ሰጥተዋል መባሉንም የዘገበው ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ነው፡፡

ተሽከርካሪዎቹን በተመለከተ ከበላይ አካል ትዕዛዝ ተላልፎላቸው እንደው የተጠየቁት፤ የወረዳው አስተዳዳሪ እና የፖሊስ አዛዥ “የደረሰን ምንም አይነት ትዕዛዝ የለም” ሲሉ አስተባብለዋል።

ድረ ገጹ ስማቸው እንዳይጠቀስ ፈልገዋል ያላቸወ አንድ የሰሜን ወሎ ዞን የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያም፤ በመቄት ወረዳው ዘጠኝ የጭነት መኪናዎች ላለፉት ሶስት ቀናት ቁመው እንደነበር መረጃ እንዳላቸው፤ “ነገር ግን ከዞን የተላለፈ ምንም አይነት ትዕዛዝ አለመኖሩን” ተናግረዋል።

በፍላቂት ገርገራ ከተማ የቆሙ የWFP የጭነት ተሽከርካሪዎችን ምስሎችን የሚያሳዩ እና በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጩ መረጃዎች፤ መኪናዎቹ ለፍተሻ ፍቃደኛ ባለመሆናቸው “መታሰራቸውን” ገልጸው ነበር።

ስለ ጉዳዩ ጥያቄ የቀረበላቸው የመቄት ወረዳ የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ቢንያም ዘውዱ፤ “መኪናዎቹ የዓለም አቀፍ ድርጅት ንብረት ስለሆኑ ወረዳው [የመፈተሽ] ሥልጣን የለውም። ምናልባት ፌደራል ፖሊስ ካልሆነ እኛ መፈተሽ አንችልም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ወዳጄም “ምንም የተፈታ ነገር የለም” ሲሉ ተሽከርካሪዎቹ በቆሙበት ወቅት ምንም አይነት ፍተሻ እንዳልተደረገባቸው ተናግረዋል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img