Tuesday, October 8, 2024
spot_img

እነ ጃዋር መሐመድ በቀጣይ ችሎቶች እንደማይገኙ አሳወቁ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ሰኔ 21፣ 2013 ― በእስር ላይ የሚገኙት የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ አመራሮቹ አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ደጀኔ ጣፋ እና አቶ ሐምዛ አዳነ ፍርድ ቤት የሚሰጠው ውሳኔ ይከበራል የሚል እምነት ስለሌላቸው በቀጣይ ችሎቶች እንደማይገኙ ለፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት 1ኛ ፀረ ሽብርና ሕገ መንግሥታዊ ወንጀሎች ችሎት በጻፉት ደብዳቤ ገልጸዋል፡፡

አራቱ ተከሳሾች በደብዳቤቸው፣ ለአገሪቱ የፍትህ ተቋም ‹‹ክብር በመስጠት›› የቀረበባቸውን ክስ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ተከራክረው ንጽህንቸውን ለማረጋገጥ በችሎት እየተገኙ ‹‹በትዕግስትና አርአያነት ባለው መልኩ ህግ አክባሪ ዜጎች›› መሆናቸውን ለማስመስከር መሞከራቸውን አስታውሰዋል፡፡

አክለውም ‹‹ይህን ስናደርግ የነበረው በችሎቱ ለተሰየሙ ዳኞች፣ ለሚያጅቡን ፖሊሶችና ለምንገኝበት ማረሚያ ቤት ተገቢውን ክብር በመስጠት ሲሆንመ በመጨረሻም ፍ/ቤቱ የሚሰጠውን ውሳኔ አስፈጻሚው የመንግስት አካል ተግባራዊ ያደርጋል በሚል ጽኑ እምነት ነበር›› ብለዋል፡፡

ነገር ግን ‹‹ከሂደቱ እንደተረዳነው ፍ/ቤቶች የሚሰጡት ውሳኔ በህገወጥ መንገድ እየተጣሰ በነፃ የተሰናበቱ ዜጎች በመንግስት ኃይሎች እየተጠለፉ ወደ ሌላ እስር ቤት ሲወሰዱ አንዳንዴም ደብዛቸው ሲጠፋ ተመልክተናል›› ያሉት ተከሳሾቹ፣ ‹‹ድርጊቱ ምናልባት አንዳንድ አስፈጻሚዎች የሚወስዱት የተናጠል የተሳሳተ እርምጃ ከሆነ ማስተካከያ እንዲደረግበት›› መወትወታቸውንም ገልጸዋል፡፡

ሆኖም ሁኔታው ከመሻሻል ይልቅ ተባብሶ ቀጥሏል በማለትም፣ በምሳሌነት ከሰሞኑ የኦነግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ጃል አብዲ ረጋሳ ከሰሞኑ ፍ/ቤት በነፃ ቢያሰናብታቸውም ከእስር ቤት ከወጡ በኃላ በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ታፍነው ወደ አልታወቀ ሥፍራ መወሰዳቸውን አመልክተዋል፡፡

በመሆኑም ‹‹የኛ እዚህ ችሎት መመላለስ የምናከብራቸው ዳኞችን፣ የጠበቆቻችንን እና የአጃቢ ፖሊሶችን ውድ ጊዜ በከንቱ ከማባከን ውጪ ፍትህን ለማስፈን አንዳች ፋይዳ አለው ብለን አንገምትም›› ያሉት እነ ጃዋር መሐመድ፣ ‹‹ይልቁንም የሌለውን ፍትህ እንዳለ በማስመሰል›› የአገሪቱን ዜጎችና ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ‹‹ማደናገር›› እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡

በዚሁ መሰረት ከዛሬ በኃላ ችሎት ላይ ‹‹በፈቃደኝነት በመገኘት በፍትህ ላይ በሚተወን ድራማ›› ሲሉ በገለጹት የፍርድ ሂደት ላይ ተሳታፊ ላለመሆን መወሰናቸውን ፍርድ ቤቱ ይወቀው ብለዋል፡፡

እነ ጃዋር መሐመድ በደብዳቤያቸው ማሳረጊያ ‹‹አስፈጻሚው አካል ለህግ የበላይነት ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር በማሳየት በፍትህ ሥርአቱ ላይ እምነት ኖሮን ወደ ችሎት የምንመላለስበት ቀን ቅርብ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን›› ሲሉ አስፍረዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img