Sunday, November 24, 2024
spot_img

በምእራብ ሸዋ ዞን ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ሦስት ሰዎች መገደላቸው ተነገረ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ሰኔ 15፣ 2013 ― በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ውስጥ ከአምቦ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ ስፍራ ትላንት ሰኞ ማለዳ ታጣቂዎች በፈጸመወው ጥቃት ሦስት ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡

በምዕራብ ሸዋ ዞን ሊበን ጃዊ ወረዳ ኖኖ ምርጫ ክልል ሥራ በሚገኙ ሁለት የምርጫ ጣቢዎች አቅራቢያ በተፈጸመው ጥቃት ሦስት ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ተቋርጦ እንደነበረ የአካባቢው የምርጫ አስፈጻሚ መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ታጣቂዎቹ በፈጸሙት ጥቃት የተገደሉት ሰዎች አንድ የአካባቢው ሚሊሻ፣ የአንድ የኦሮሚያ ፖሊስ አባል እና አንድ የአካባቢው ባለሥልጣን መሆናቸውን ተገልጿል።

ትናንት ምሽት የምርጫውን አፈጻጸም አስመልክቶ ለጋዜጠኞች የተናገሩት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ፣ በአካባቢው መጠነኛ ችግር ተከስቶ እንደነበር ጠቁመው ነበር።

‹‹በምዕራብ ሸዋ ኖኖ ምርጫ ክልል ሁለት ጣቢያዎች ላይ የታጠቁ ሰዎች ሂደቱን ረብሸው የድምጽ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓቱ ተቋርጦ ነበረ›› ብለዋል። ሰብሳቢዋ አክለውም ‹‹ከዚህ ውጪ ይህ ነው የሚባል የጸጥታ ችግር የለም›› ብለዋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ጥቃቱ የተፈጸመበት አካባቢ የምርጫ ቦርድ ኃላፊ ለቢቢሲ እንዳብራሩት ታጣቂዎቹ በከፈቱት ተኩስ ሦስት ሰዎች ተገድለው ድምጽ አሰጣጡ ተቋርጦ እንደነበር አረጋግጠዋል።

እንደ አካባቢው ምርጫ አስፈጻሚ በሊበን ጃዊ ወረዳ አገል ጎቦ ተብሎ በሚጠራው መንደር ውስጥ ሰኞ ጠዋት ከሦስት ሰዓት በኋላ ነው ታጣቂዎቹ ጥቃቱን ፈጽመው ሰዎች የገደሉት።

በአካባቢው ባሉ ‹‹ሁለት የምርጫ ጣቢዎች መካከል ነው ችግሩ የተከሰተው›› ያሉት የአካባቢው የምርጫ ኃላፊ፤ ሁለቱ የምርጫ ጣቢያዎች ኑኑ ባሳሌ እና አጋል ጎቦ እንደሚባሉም ተናግረዋል።

የምዕራብ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ዲሪርሳ ዋቁማ በታጣቂዎች ጥቃቱ መፈጸሙን አረጋግጠው፤ ‹‹ታጣቂዎች ከእሁድ ምሽት ጀምረው ምርጫው መከናወን የለበትም በማለት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ነበር›› ብለዋል።

ባለፈው ሳምንት በዚሁ በምዕራብ ሸዋ ዞን ውስጥ ሜታ ወልቂጤ ተብላ በምትጠራ ወረዳ ውስጥ የሸኔ ታጣቂዎች ፈጸሙት በተባለው ጥቃት ቢያንስ 9 በአካባቢው በመንገድ ግንባታ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።

ጥቃቱን አድርሷል የተባለው ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር ተለይቶ የወጣውና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ቡድን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ተብሎ የተሰየመ ሲሆን፤ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ከሚፈጸሙ ግድያዎችና ጥቃቶች ጋር ስሙ በተደጋጋሚ ይነሳል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img