Sunday, November 24, 2024
spot_img

ዐቃቤ ሕግ በላምሮት ከማል ላይ የተሰጠው ብይን ማስረጃን ያላገናዘበ ነው አለ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ሰኔ 9፣ 2013 ― ዐቃቤ ሕግ ተልእኮ ተቀብላ አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ገላን ኮንዶሚኒዬም በመውሰድ የግድያ ቦታ አመቻችታለች ተብላ የተከሰሰችው ላምሮት ከማል ላይ በስር ፍርድ ቤት የተሰጠው ብይን ማስረጃን ያላገናዘበ ነው ብሏል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ይህን ያለው በዛሬው በጠቅላይ ፍርድ ቤት 2ኛ ይግባኝ ሰሚ ችሎት በነበረ ክርክር ወቅት ነው፡፡

ተከሳሽ ላምሮት ከማልን ከ2 ወር በፊት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ የፀረ ሽብርና ህገ መንግስት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በተከሰሰችበት ወንጀል የቀረበው የሰውና የሰነድ ማስረጃ ወንጀሉን ለመፈፀሟ አያስረዳም ሲል በነጻ አሰናብቷት እንደነበር ይታወቃል፡፡

ሆኖም ዓቃቢህግ በስር ፍርድ ቤት ነፃ ብሎ የሰጠው ብይን ተገቢነት የሌለው ነው ሲል ለጠቅላይ ፍ/ቤት 2ኛ ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ ማለቱን ተከትሎ በግንቦት 23፣ 2013 የይግባኝ ሰሚ ችሎቱ በነበረው ቀጠሮ ለማከራከር የተሰየመ ቢሆንም የቃሊቲ ማረሚያ ቤት መብራት በመጥፋቱ እና ተከሳሿ ላምሮት በፕላዝማ ቀርባ ሐሳቧን ለማቅረብ ጥያቄ ማቅረቧን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ ለዛሬ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር፡፡

በዚህም በዛሬው ቀጠሮ ይግባኝ ባይ ዓቃቤ ሕግ ተከሳሿ ከኦነግ ሸኔ አባል ጋር ሜክሲኮ ተገናኝታ ተልኮ ተቀብላ ሀጫሉን ወደ ሚገደልበት ቦታ አመቻችታ መውሰዷን የሚገልጽ ማስረጃ እንዳለው በመጠቆም፣ የስር ፍርድ ቤቱ ድርጊቱ የሽብር ወንጀል መፈፀሙን ገልጾ እያለ በሌላ በኩል ደግሞ ተከሳሿን ነጻ ማለቱ የሚጣረስና አግባብነት የለውም ሲል መከራከሪያ ነጥብ አንስቷል፡፡

ፍርድ ቤቱም በወቅቱ ያልተመዘነ ማስረጃ አለ ወይ ብሎ ላቀረበው ጥያቄ የድርጊቱ አፈጻጸም በራሱ የሽብር ወንጀል ነው በግድያው ወቅትም አብራ ነበረች ሲል ምላሽ ሰጥቷል፡፡

የተከሳሿ ተከላካይ ጠበቃም የስር ፍርድ ቤት ብይን ተገቢነት ያለው ነው፣ ማስረጃወም ተመዝኖ ነው ብይኑን የሰጠው፣ ብይኑ ሊነቀፍ አይገባም በማለት፣ ሟች እንደተገደለ ለምስክሩ ደውላ መናገሯን እና በወቅቱ ቦታውን አላወቅኩም ብላ በአካባቢው ለነበረ ሰው ስልክ ማገናኘቷን ጠቅሶ፣ በቦታው ስለተገኘች ብቻ ወንጀለኛ ልትባል አይገባም ሲል ምላሽ ሰጥቷል፡፡

ፍርድ ቤቱም ለላምሮት ጓደኛሽ ሲገደል በአካባቢው ያሉ ሰዎችን ለምን ጮኸሽ አልተጣራሽም ብሎ የማጣሪያ ጥያቄ ያቀረበላት ሲሆን፣ ላምሮት ከማልም በወቅቱ ስጮህ በአካባቢው ሰው የለም ለዛ ነው ለጓደኛዬ የደወልኩት ስትል ምላሽ ሰጥታለች፡፡

ከየት ነው የተነሳችሁት ስትባል ከሜክሲኮ ነው የተነሳነው እና የሄድነው ብላለች፡፡
ከአርቲስት ሀጫሉ ጋር በሳምንት ሶስት ሁለት ጊዜ እንገናኛለን ጓደኛዬ ነው ስትልም አስረድታለች፡፡ ተከሳሽ በወቅቱ እኔም እግሬ በጥይት ተመትቼ ነበር ብላ ተደምጣለች፡፡

ፍርድ ቤቱም መርምሮ ብይን ለመስጠት ለሀምሌ 5፣ 2013 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰቷል፡፡
በችሎተ የሀጫሉ ሁንዴሳ ባለቤትና የተከሳሽ ላምሮት እህት ተገኝተው ታድመዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img