አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ሰኔ 2፣ 2013 ― የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ይህን የገለጹት ‹‹በስራ እንጂ በአሉባልታ ስም ማጥፋት ያደገ ሀገር የለም›› ባሉት ዘለግ ባለው ከሰሞኑ የሚመሩት የከተማው አስተዳደር ፕሮፐርቲ2000 ከተባለ የደቡብ አፍሪካ የቤት አልሚ ኩባንያ ጋር ያደረገው ስምምነት አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ ነው፡፡
ጠንከር ያሉ ቃላት ባዘለው ማብራሪያቸው ወይዘሮ አዳነች የአዲስ አበባን የቤት እጥረት ለመፍታት አደረግነው ያለትን ጥናት ተከትሎ ‹‹ከብዙ ድርድርድና ውይይት በኋላ በብዙ መመዘኛዎች ሁሉት አለም አቀፍ አልሚዎች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ መኖሪያ ቤቶችን አነስተኛ ገቢ ላላቸው ለመንግስተ ሠራተኞች፤ ተመዝግበው የቤት ባለቤትነትን እየጠበቀ ላሉ ነዋሪዎች ለመገንባት›› ከስምነት መደረሱን ገልጸዋል፡፡
ሆኖም ከነዚህ መካከል የሆነው ፕሮፐርቲ2000 ላይ ‹‹የህዝባችንን ለዘመናት ሰሚ ያጣ ጥያቄ ለመመለስ ሌት ተቀን ስንሰራ አይናቸው የሚቀላ፤ ተሳዳቢዎች፤ ስም-ማጥፋት እንጂ፤ ሰርተው ማሳየት ያልቻሉ፤ በስራ ሳይሆን በወሬ ስብእናቸውን ለመገንባት የሚጥሩ፤ ለኢትዮጵያ ህዝብ አንዲት ነገር ሰርተው ማሳየት ያልቻሉ አዋቂ ነን ባዮች የሆኑ ጥቂቶች ይህንን ጥረታችንን፤ ስራችንን ለማጠልሸት እና ህዝቡን ለማደናገር ሲሞክሩ ተመልክተናል›› ብለዋል፡፡
ወይዘሮ አዳነች ሥም ማጥፋት ተፈጽሞበታል ካሉት ኩባንያ ጋር የከተማ አስተዳደሩ የገባውን ውል አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፣ 500 ሺሕ ቤቶችን የሚገነባው አልሚ ‹‹ለግንባታው የሚያስፈልገውን 4 ነጥብ 2 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ካፖኒው ከውጪ ይዞት ለመምጣት እንጂ ከእኛ ባንኮች ምንም አይነት የሚፈልግ ብድር አልፈረምንም›› ሲሉ አስፍረዋል፡፡
በተጨማሪም ‹‹አልሚው በመጀመሪያ የግንባታ ምዕራፍ ለሚገነባው 100 ሺሕ ቤቶች ግንባታ የሚውል 500 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገንዘብ ያዘጋጀ ስለመሆኑ ህጋዊ ሠነዶችን አቅርቧል›› ያሉት ወይዘሮ አዳነች፣ ‹‹በእኛ በኩል ደግሞ ለግንባታው የሚያስፈልገውን መሬት በአስተዳደሩ ስር ሆኖ ለግንባታ እንዲቀርብ በተጨማሪም ለግንባታ የሚያስፈልጉ ግብአቶችን ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገባ የምንፈቅድ ሲሆን፣ በተጨማሪም ቤቶቹን ገንብቶ ካስረከበን በኋላ በ30 ዓመት ውስጥ የግንባታውን ዋጋ ትርፍና ወለድ ለመክፈል ግዴታ መግባት ሲሆን በስምምነቱን መሠረት ለግንባታ የሚያስልገው መሬት በአስተዳደሩ ባለቤትነት ስር የሚቆይ እንጂ ለአልሚው ድርጅት የሚተላለፍ አይደለም›› ማለታቸው ተመላክቷል፡፡
ወይዘሮ አዳነች ‹‹እኛም ካለን በርካታ አማራጮች መካከል አንዱ እንጂ ብቸኛው አማራጭ አይደለም›› ካሉት ፕሮፐርቲ2000 ጋር ከተደረገው ስምምነት ሂደት ‹‹የምናተርፈው፤ የምናዳብረው፤ እንጂ የምናጣው እንዳች ነገር›› እንደሌለ ገልጸዋል፡፡
አክለውም ፕሮፐርቲ2000 በስምምነቱ መሠረት ቤቶችን ይገነባል ብለን ተስፋ እናደርጋለን ያሉ ሲሆን፣ ‹‹ባይገነባም ደግሞ አስቀድመን አማራጮችን ይዘናል፤ በሚቀጥሉት 5 ዓመታትም 1 ሚሊዮን ቤቶች እንገነባለን›› ሲሉ አሳርገዋል፡፡