Saturday, November 23, 2024
spot_img

እነ እስክንድር ነጋ ለመጪው ምርጫ በእጩነት ተመዘገቡ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ግንቦት 27፣ 2013 ― በእስር ላይ የሚገኙት የባልደራስ ሊቀመንበር አቶ እስክንድር ነጋ ጨምሮ አራት የፓርቲው አመራር አባላት በመጪው ምርጫ በእጩነት ተመዝግበዋል፡፡

አቶ እስክንድር ነጋን ጨምሮ አቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ አስካለ ደምሌ እና ቀለብ ሥዩም በምርጫው የተመዘገቡት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በምርጫ እንዲወዳደሩ ውሳኔ ከሰጠ በኋላ ነው፡፡

ባልደራስ ቀድሞ አሁን የተመዘገቡ በእስር የሚገኙ አራት አመራሮቹን በዕጩነት ለማስመዘገብ ጠይቆ በምርጫ ቦርድ ተቀባይነት ሳይገኝ ከቀረ በኋላ፤ በእነርሱ ምትክ ሌሎች አባላቱን አስመዝግቦ የነበረ ሲሆን፣ እነዚህ ተተኪ ዕጩዎች በየካ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ ኮልፌ ቀራንዮ እና አቃቂ ቃሊቲ የምርጫ ክልሎች ለአዲስ አበባ ምክር ቤት ለመወዳደር በምረጡኝ ቅስቀሳ ላይ ቆይተዋል።

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የምርጫ ቦርድ ውሳኔን ውድቅ ካደረገ በኋላ ግን በእነዚህ የምርጫ ክልሎች የተመዘገቡ አራት ዕጩዎች በእስር ላይ በሚገኙት የባልደራስ አመራሮች ተተክተዋል። የባልደራስ ሊቀመንበር አቶ እስክንድር ነጋ የተኳቸው በየካ ምርጫ ክልል የተመዘገቡትን አቶ አለማየሁ አበበን መሆኑ ተሰምቷል፡፡

የፓርቲው የድርጅት ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ቸኮል በሚወዳደሩበት የንፋስ ስልክ ላፍቶ የምርጫ ክልል ለአዲስ አበባ ምክር ቤት ለውድድር የቀረቡት አቶ ደምሌ አባተ እንዲሁ በተመሳሳይ ሁኔታ ዕጩነታቸውን ማስረከባቸው ነው የተገለጸው፡፡

የባልደራስ የሴቶች ጉዳይ ኃላፊ አስካለ ደምሌ ለዕጩነት በቀረቡበት በኮልፌ ቀራንዮ ምርጫ ክልል ከተወዳዳሪነት የተሰናበቱት አቶ ይልቃል ሙሉዬ መሆናቸው ተነግሯል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img