አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ግንቦት 27፣ 2013 ― የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከትላንት በስትያ ግንቦት 25፣ 2013 በከተማው 500 ሺሕ ቤቶች እንዲገነባለት የተፈራረመው የደቡብ አፍሪካው ‹ፕሮፐርቲ 2000› የተሰኘ ኩባንያ በዘርፉ ላይ 2 ዓመት ከግማሽ ብቻ ልምድ ያለው መሆኑን ስለ ድርጅቱ የተጻፉ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
በደቡብ አፍሪካ ብሎምፎንቴን ከተማ የተመዘገበው ፕሮፐርቲ 2000፣ በኢትዮጵያ የዘመን ቀመር ኅዳር ወር 2011 የተመዘገበ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም በምእራብ አፍሪካዊቷ ሌሴቶ ከስታዲየም ግንባታ ጋር በተገናኘ ለሦስት የአገሪቱ ተቋራጮች ብድር ለማመቻቸት ገንዘቡን እቀበልበታለሁ ያለው የእንግሊዝ ባንክ ያልተመዘገበ ነው በሚል ውሉ የተሰረዘበት መሆኑም ነው የታወቀው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አሁን ባደረገው ስምምነት ኩባንያው ይገነባልኛል ላለው 500 ሺሕ ቤት፣ ከ4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በላይ በጀት መያዙን አስታውቋል፡፡
የፕሮፐርቲ 2000 ኩባንያ ስራ አስኪያጅ ናፒ ኤዲ ሞዲሴ በኢትዮጵያ ባለውን ምቹ አስትዳደር ለስራ እንድንመጣ አድርጎናል ማለታቸውን የከተማው መስተዳደር ጽሕፈት ቤት ገልጾ ነበር፡፡
ኩባንያው በቤቶቹ ግንባታ በርካታ ሥራ እንደሚፈጠርና 90 በመቶ ያህሉ ሠራተኛችም ኢትዮጵያውያን እንደሚደርግ የኩባንው ሥራ አስኪያጅ ተናግረዋል፡፡
ኩባንያው በመጀመሪያ ምእራፍ 100 ሺሕ ቤት እንደሚገነባም የከተማው ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በስምምነቱ ላይ ገልፀዋል።
የዚሁ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አዴ ናፖ በዛሬ እለት ሞዴሳ ከከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሚኒስትር አይሻ መሐመድ ጋር ተገናኝተው የሚመሩት ኩባንያ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ኢንቨስትመንቱን በክልሎችም ለማስፋፋት ዕቅድ እንዳለው መናገራቸውን የመንግሥት ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡