አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ግንቦት 25፣ 2013 ― የከተማ አስተዳደሩ 500 ሺሕ ቤት እንዲገነባልኝ ተስማምተናል ያለው ከደቡብ አፍሪካው ፕሮፐርቲ 2000 ከተሰኘ ኩባንያ ጋር ነው፡፡
ኩባንያው በመጀመሪያ ምእራፍ 100 ሺሕ ቤት እንደሚገነባም የከተማው ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልፀዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ የሚስተዋለውን የቤት እጥረት ለመፍታት በቀጣይ አምስት ጊዜ ውስጥ ከ1 ሚሊየን በላይ ቤቶችን ለመገንባት እየሰራን ነው ያሉት ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ ከደቡብ አፍሪካው ፕሮፐርቲ 2000 ኩባንያ ጋር ዛሬ የተደረገው ስምምነት የእቅዳችን አካል ነው ማለታቸውንም የከተማው አስተዳደር ጽሕፈት ቤት በፌስቡክ ገጹ ላይ አስታውቋል፡፡
አክለውም በደቡብ አፍሪካው ፕሮፐርቲ 2000 ኩባንያ የሚገነቡት 500 ሺህ ቤቶች በዝቅትኛ ወለድና በረጅም ጊዜ ክፍያ ለተጠቃሚዎች የሚቅርቡ ናቸው ያሉ ሲሆን፣ የከተማ አስትዳዳሩም ከመሬት አቅርቦት ጀምሮ የመሠረተ ልማት እና ሌሎች አስፈላጊው ግብዓት ለማቅረብ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።
የፕሮፐርቲ 2000 ኩባንያ ስራ አስኪያጅ ናፒ ኤዲ ሞዲሴ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ባለውን ምቹ አስትዳደር ለስራ እንድንመጣ አድርጉናል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዝቅትኛ ወለድና በረዥም ጊዜ ክፍያ ለተጠቃሚዎች ይቀርባል ላለው የቤቶቹ ግንባታ ከ4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በጀት መያዙን ገልጿል።